መረጃዎች | 106ኛ የጨዋታ ቀን

የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ምክንያት ከመቋረጡ በፊት የሚደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።

ወልቂጤ ከተማ ከ መቻል

ዛሬ ከተካሄደው ጠንካራ ጨዋታ ቀጥሎ የሳምንቱ ትልቅ ጨዋታ የሆነው እና ሁለት በሊጉ ለመትረፍ በጥረት ላይ የሚገኙ ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች መድንን አሸንፈው ከፋሲል ከነማ አቻ የተለያዩት ወልቂጤዎች በመጨረሻዎቹ አስር ጨዋታዎቹ የወጥነት ችግር ታይቶባቸዋል።
ከአስሩ ጨዋታዎች በአራቱ ሽንፈት፤ በሦስቱ ድል እና በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ደሞ አቻ ተለያይተዋል። በጊዜ ሂደት የተከላካይ ክፍላቸው ላይ መሻሻሎች ያሳዩት እና ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች በአንዱ ጨዋታ ብቻ ግብ ያስተናገዱት ወልቂጤዎች በተጠቀሱት ጨዋታዎች በወሳኝ ወቅት የግብ ማግባት ችግር ገጥሟቸው ነበር። ይህ ክፍተት በነገው ጨዋታ የሚቀጥል ከሆነም ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት አስቸጋሪ ሊያደርግባቸው ይችላል። በሠላሳ ሦስት ነጥብ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ሰራተኞቹ ከዚህ ጨዋታ በኋላ ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማን ይገጥማሉ።

\"\"

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተንሸራተቱ ወደ ወራጅ ቀጠናው የተጠጉት መቻሎች እንደ ተጋጣሚያቸው በተመሳሳይ ከፍተኛ የወራጅነት ስጋት አንዣቦባቸዋል። ከተጋጣምያቸው አንፃር የተሻለ የአማካይ ተጫዋቾች ጥራት ያላቸው መቻሎች በዚህ ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ይወስዳሉ ተብሎ ቢጠበቅም በባለፉት አራት ጨዋታዎች በአንዱ ጨዋታ ብቻ መረቡን ያስደፈረው የወልቂጤ የመከላከል አደረጃጀት መስበር ቀላል አይሆንላቸውም። መቻሎች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ ላይ በተከታታይ ድል ከተቀዳጁ በኋላ ባካሄዷቸው አራት ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ ማግኘት አልቻሉም። ይህንን ተከትሎም ደረጃቸው ሊያሽቆለቁል ችሏል። በነገው ጨዋታም የቅርብ ተቀናቃኛቸው ላይ ድል መቀዳጀት ያለው ትርጉም ትልቅ እንደ መሆኑ ለጨዋታው ትልቅ ግምት ሰጥተው እንደሚገቡ እሙን ነው። ይህ እንዲሆን ግን ባለፈው ከባህር ዳር ከተማ ጋር ትልቅ የትኩረት ማጣት ችግር የተስተዋለበት ስብስብ በአዕምሮ ደረጃ ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል።

ወልቂጤዎች አማካዩ አፈወርቅ ኃይሉ በጉዳት አያሰልፉም ፤ በተቃራኒው ውሀብ አዳምስ ከቅጣት ይመለስላቸዋል። በመቻል በኩል ኢብራሂም ሁሴን ፣ ቹል ላም እና ፍፁም ዓለሙ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም።

ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ መድን

በነገው ዕለት የሚካሄደው ሁለተኛ እና የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

በጥሩ ወቅታዊ አቋም የማይገኙት ፋሲል ከነማዎች ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነው ድል ማድረግ የቻሉት። በተጠቀሱት ጨዋታዎች ሁለት አቻ እና ሁለት ሽንፈቶች አስተናግደዋል። በሁነኛ አጥቂ እጦት ምክንያት ጨዋታዎች ለማሸነፍ ሲቸገሩ የተስተዋሉት ዐፄዎቹ መጨረሻ ካደረጓቸው አስር ጨዋታዎች በሁለቱም ብቻ ነው ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር የቻሉት። የተሻለ የፈጠራ አቅም ያለው አማካይ ክፍል ያላቸው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም ይህንን የግብ ማግባት ችግር ለመቅረፍ በአጥቂ ክፍሉ ላይ የግድ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የነገው ተጋጣምያቸው ኢትዮጵያ መድን ግቦች ለማስቆጠር የማይሰንፍ ቡድን መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ የቡድኑ ተከላካይ ክፍል ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠጣር እና ጠንቃቃ መሆን ይጠበቅበታል።

\"\"

በውድድር ዓመቱ ጠንካራ የዋንጫ ተፎካካሪ የነበሩት መድኖች ልፋታቸውን ቢያንስ ቢያንስ በሜዳሊያ ለማጀብ የነገው ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ምንም እንኳ የተወሰነ የወጥነት ችግር ቢታይበትም በርካታ ግቦች ለማስቆጠር የማይቸገር ስል የአጥቂ ክፍ ይዟል። ባለፉት አስር ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ሀያ ግቦች (በአማካይ በጨዋታ 2 ግብ) የቡድኑ የአጥቂ ክፍል ምን ያህን አስፈሪ እንደሆነ ማሳያ ናቸው። ሆኖም የቡድኑ የመከላከል ክፍል እንደ ሌሎች የቡድኑ ክፍሎች ጠንካራና ጠጣር ባለመሆኑ ጨዋታዎች እንዳያሸንፉ አድርጎታል። ቡድኑም በመጨረሻዎቹ አስር ጨዋታዎች አስራ ሦስት ግቦች ተቆጥረውበታል። ቡድን በነገው ጨዋታ ጨምሮ በቀጣይ ጨዋታዎች ይህንን የቡድኑ ደካማ ጎን ማሻሻል ይጠበቅበታል።

በጨዋታው በዐፄዎቹ በኩል በዛብህ መለዮ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ በጉዳት አይሰለፉም። ታፈሰ ሰለሞንም ከቡድኑ ጋር አይገኝም። መድኖች ግን በቅጣትም በጉዳትም የሚያጡት ተጫዋች የለም።