የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ነገ ይጀመራል

ወደ 2016 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር የሚያድጉ አራት ክለቦችን ለመለየት የሚደረገው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ነገ ከመጀመሩ በፊት በዛሬው ዕለት የዕጣ ማውጣት መርሐ-ግብር ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚከናወነው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ከነገ ሰኔ 14 ጀምሮ የ2015 ውድድሩን በሲዳማ ክልል በሀዋሳ ከተማ አስተናጋጅነት እስከ ሐምሌ 8 ድረስ እየተደረገ ይቆያል። በ2016 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ አራት ክለቦች የሚለዩበት ይህ ውድድር በ31 ቡድኖች መካከል በነገው ዕለት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ላይ ከመጀመሩ አስቀድሞ በዛሬው ዕለት በሲዳማ ባህል አዳራሽ ከአመሻሽ 11፡00 ጀምሮ የዕጣ ማውጣት መርሐ-ግብር ተካሂዷል።
\"\"
በዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓቱ ላይ አቶ ከበደ ወርቁ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የውድድር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ፣ የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ እንዲሁም የዳኞች ኮሚቴ ተወካዩ ክንዴ ሙሴን ጨምሮ የውድድር ኮሚቴዎች እና የክለብ ተወካዮች በተገኙበት ተከናውኗል። አቶ አንበሴ አበበ የሲዳማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ፕሮግራሙ ከተከፈተ በኋላ ከክለቦች ጋር ውይይት ተደርጓል። ውይይቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከአማራ ክልል የተወከለው የደብረ ታቦር ከተማ ክለብ አስፈላጊውን ክፍያ በመክፈል ለውድድሩ የቀረቡ ቢሆንም የክልሉ እግር ኳስ ፌድሬሽን ለሀገር አቀፉ ፌዴሬሽን ስማቸውን አለማስተላለፉን ተከትሎ ከውድድር ውጪ በመሆናቸው ቅሬታቸውን በአዳራሹ ቢያሰሙም ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል። በመቀጠል ተወዳዳሪ ክለቦች የገጠማቸውን ችግሮች እና በውድድሩ ላይ መደረግ አሉባቸው ያሏቸውን በርካታ ጉዳዮች በጥያቄ መልኩ ማንሳት ከቻሉ በኋላ በአወዳዳሪው እና በየዘርፉ በተመረጡ ኮሚቴዎች ምላሽ ተሰጥቶ በመጨረሻም በውድድሩ ፀሀፊ አለሙ ኤሮሞ መሪነት የዕጣ ማውጣት ሒደቱ ከተመራ በኋላ የምድብ ድልድሉ ይፋ ሆኗል።

\"\"

ምድብ 1 – 5ኛ ካምፕ ሀዋሳ ፣ ሚቶ ፣ ኩርሙ ጉሌ ፣ ቤሮ ወርቅ

ምድብ 2 – ቃላድ አምባ ፣ ጎንደር አራዳ ፣ ወንዶ ገነት ፣ መንጌ ቤላሻንጉል

ምድብ 3 – ናቲ ዩኒቲ ፣ ቡልቡላ አሜን ፣ ዋልያ ድሬዳዋ ፣ ሱሉልታ ቢ

ምድብ 4 – አማያ ፣ ቦሌ ገርጂ ፣ ገንደ አብዲ ቦሩ ፣ ዱል አዛሀቢ

ምድብ 5 – መታፈሪያ ክፍሌ ፣ ደምበጫ ከተማ ፣ ቢኢ ከተማ ፣ ማያ ሲቲ

ምድብ 6 – ጊምቦ ዳዲበን ፣ ኛንግላንድ ፣ መልካ ኖኖ ፣ ፍቅር በአንድነት

ምድብ 7 – ቦረና መካነ ሰላም ፣ ጊምቢ ከተማ ፣ አርባምንጭ ዙሪያ ፣ ሠመራ ሎጊያ

ምድብ 8 – ቲሊሊ ከተማ ፣ ደንቢ ዶሎ ፣ የኛ አዲስ ከቴ
\"\"
ነገ ሁለት የመክፈቻ ጨዋታዎች ሲኖሩ 5ኛ ካምፕ ሀዋሳ ከ ኩርሙ 4 ሰዓት በመቀጠል ቀትር 6 ሰዓት ላይ ሚቶ ከ ቢሮ ወርቅ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ላይ እንደሚያደርጉ ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ ለማወቅ ችላለች።

በተያያዘ የሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በነገው ዕለት የዕጣ ማውጣት መርሐ-ግብር ከተካሄደበት በኋላ ሐሙስ ውድድሩ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ እንደሚጀምርም ታውቋል።