ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ የነበረው ተስፋ አብቅቷል

አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ መድንን 3-0 በመርታት ደረጃውን አሻሽሏል።

\"\"

የዕለቱ መርሐግብር 9 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ባደረጉት ጨዋታ ሲጀመር ሁለቱም ቡድኖች በሚያሳዩት ማራኪ የኳስ ቅብብል መጠነኛ ፉክክር የተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ 17ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ መድን አማካኝነት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ተደርጎበታል። ሳይመን ፒተር ከመስዑድ መሐመድ በቀማው ኳስ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ መውጣቱን ተመልክቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ወደ ቦታው ተመልሶ ኳሱን ይዞበታል። 

ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት አዳማዎች 21ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ዮሴፍ ታረቀኝ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው ዳዋ ሆቴሳ ኳሱን አክርሮ በመምታት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም አቡበከር ኑራ እና የግቡ የላይ አግዳሚ መልሰውበታል።

እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት መድኖች 27ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን የግብ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ቴዎድሮስ በቀለ በግንባሩ ገጭቶ ያቀበለውን ኳስ ባሲሩ ኦማር ከጨዋታ ውጪ ነኝ ብሎ በማሰብ እና ዘግይቶም ኳሱን ለመቆጣጠር በመሞከር የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ሲቀር በ 20 ሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ አዳማዎች በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በዚህም አማኑኤል ጎበና ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

\"\"

ከራሳቸው የግብ ክልል በፍጥነት በመውጣት ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ማድረግ የቀጠሉት አዳማዎች 30ኛው ደቂቃ ላይም በዳዋ ሆቴሳ አማካኝነት ግሩም የግብ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። የመሃል ተከላካዩ ሀቢብ መሐመድ በግንባሩ ገጭቶ በትክክል ያላራቀውን ኳስ ያገኘው ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በግሩም ቅልጥፍና ሲያስወጣበት በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ግን አዳማዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። መስዑድ መሐመድ ከቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻገረለትን ኳስ ከሳጥን ውጪ ከረጅም ርቀት ላይ ሆኖ የተቀበለው የግራ መስመር ተከላካዩ ደስታ ዮሐንስ ኳሱን ለቀኝ እግሩ አመቻችቶ አክርሮ በመምታት እጅግ ድንቅ ግብ አድርጎታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል መድኖች የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ይቸገሩ እንጂ ወደፊት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተሻለ መነቃቃት ማሳየት ችለው ነበር። ሆኖም በአጋማሹ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተቀዛቅዘው የነበሩት አዳማዎች 63ኛው ደቂቃ ላይ በፉዓድ ኢብራሂም አማካኝነት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በቀላሉ ይዞታል።

ጨዋታው 78ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን አዳማዎች ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። አማኑኤል ጎበና ወደ ጎን ለማቀበል የሞከረውን ኳስ ሀብታሙ ሸዋለም ተደርቦ ሲመልስበት ኳሱ አቅጣጫ ቀይሮ ወደ ኢትዮጵያ መድን የግብ ክልል ሲሄድ ያገኘው ታዳጊው ቢኒያም ዓይተን ከአብዱልከሪም መሐመድ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ግብ ጠባቂው ባሰፋበት የግቡ አቅጣጫ በግሩም የአጨራረስ ብልጠት በመምታት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከሚታወቁበት አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እጅግ ተዳክመው የቀረቡት መድኖች 86ኛው ደቂቃ ላይም በተዘናጉበት ቅፅበት ተጨማሪ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። ኤልያስ ለገሠ ከቢንያም ዓይተን የተሻገረለትን ኳስ በቀኙ የሳጥኑ ክፍል አስጨናቂ ፀጋዬን አታልሎ በማለፍ ይዞት ገብቶ ወደ ውስጥ ሲያሻገር በዳዋ ሆቴሳ እና አብዱልከሪም መሐመድ ተጨርፎ ግብ ሆኗል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ለይኩን ታደሰ ዛሬ ተቀዛቅዘው እንደቀረቡ እና መጥፎ ከነበሩባቸው ቀኖች አንዱ እንደሆነ ሲገልጹ ብልጫ ተወስዶባቸው ሳይሆን በራሳቸው ስህተት ግብ እንደተቆጠረባቸው ተናግረዋል። የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሡ እንዳለ በበኩላቸው የመሃል ሜዳውን ክፍል ለመቆጣጠር ፈልገው እንደተሳካላቸው በመናገር ቢኒያም ዓይተን ያስቆጠረው ግብ የጭንቅላት ደረጃውን የሚያሳይ እንደሆነ አድናቆታቸውን በመግለጽ ዓላማቸው ከ40 ነጥቦች በላይ ማሳካት በመሆኑ ለቀጣዩ ጨዋታም ጠንክረው እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።