ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ለገጣፎ ለገዳዲ ከጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር ሲዳማ ቡናን 3-2 መርታት ችሏል።
9 ሰዓት ላይ የለገጣፎ ለገዳዲ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ሲደረግ ለገጣፎዎች ከሊጉ መውረዳቸውን ሲዳማዎች በአንጻሩ ከሊጉ መትረፋቸውን በማረጋገጣቸው እና ከጫና ነጻ ሆነው መጫወትን በመምረጣቸው ብዙም ፈጣን የሆነ የማጥቃት ሽግግር ያልታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል። የጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራም 19ኛው ደቂቃ ላይ በለገጣፎዎች አማካኝነት ሲደረግ ቴዲ ንጉሡ ከተፈራ አንለይ የተሻገረለ እና ከቀኝ መስመር ያሻማው ኳስ አቅጣጫ ቀይሮ ወደ ግብ ሲያመራ ግብ ጠባቂው አዱኛ ጸጋዬ አስወጥቶታል። ያንኑ ኳስ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ሲሻማ ያገኘው ካርሎስ ዳምጠው በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎት ለገጣፎን መሪ ማድረግ ችሏል።
የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በተቸገሩት ሲዳማዎች በኩል አበባየሁ ዮሐንስ 27ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት እና 31ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት ሁለት ሙከራዎችን አድርጎ የመጀመሪያ ሙከራው በቀኙ የግቡ ቋሚ በኩል ሲወጣበት ሁለተኛ ሙከራውን ግብ ጠባቂው ኮፊ ሜንሳህ መልሶበታል። እየተቀዛቀዘ በቀጠለው ጨዋታም 41ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ በለገጣፎዎች አማካኝነት ሲቆጠር አማኑኤል አረቦ ግብ ጠባቂው አዱኛ ጸጋዬ በግንባሩ በመግጨት ያራቀውን ኳስ በመቆጣጠር በተረጋጋ ሁኔታ ቦታ ዓይቶ ግብ አድርጎታል።
ከዕረፍት መልስ ሲዳማዎች የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም የጠራ የግብ ዕድል ፍለጋ ጥረት በሚያደርጉ ሰዓት 62ኛው ደቂቃ ላይ በሱለይማን ትራኦሬ ተጨማሪ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። ሆኖም ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግ የቀጠሉት ለገዳዲዎች 65ኛው ደቂቃ ላይም በአማኑኤል አረቦ አማካኝነት ተጨማሪ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው አዱኛ ጸጋዬ ተመልሶባቸዋል።
በሰፊ የግብ ልዩነት ብልጫ ቢወሰድባቸውም ተስፋ ባለመቁረጥ በተረጋጋ የማጥቃት ሂደት መጫወት የቀጠሉት ሲዳማዎች 70ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ግብ አስቆጥረዋል። የመሃል ተከላካዩ ያኩቡ መሐመድ ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ በተቃራኒ ቡድን ተጫዋች ተጨርፎ መረቡ ላይ አርፏል። 79ኛው ደቂቃ ላይም መሃሪ መና ከቅጣት ምት ግሩም ሙከራ አድርጎ በግብ ጠባቂው ኮፊ ሜንሳህ እና በግቡ የላይ አግዳሚ ተመልሶበታል።
በለገጣፎ በኩል ውጤቱን ለማስጠበቅ በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚደረገው ፉክክር እየጨመረ በሄደባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች 86ኛው ደቂቃ ላይ መሃሪ መና በግራ መስመር ከማዕዘን በተሻገረ እና በተከላካዮች በደንብ ባልራቀ ኳስ ያገኘውን የግብ ዕድል ተጠቅሞ ተጨማሪ ግብ ሲያስቆጥር ድራማዊ ክስተት እየታየ በሄደበት ጨዋታ 90ኛው ደቂቃ ላይ የለገጣፎው አጥቂ ሱለይማን ትራኦሬ የሲዳማን ግብ ጠባቂ አዱኛ ጸጋዬን በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። ይህም የመጨረሻው ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በለገጣፎ ለገዳዲ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ለወጣቶች ዕድል የሰጡበት ጨዋታ እንደነበር እና ተከላካዩ መኳንንት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እንዳደረገ በመናገር ቀጣዩ ጨዋታ ላይ ከውጤቱ ባሻገር ወጣቶች ዕድል በመስጠት በድል ለመወጣት እንደሚሞክሩ ሲገልጹ የለገጣፎ ለገዳዲው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው ተጫዋቾችን በአእምሮ አዘጋጅቷቸው እንደነበር በመግለጽ በመጀመሪያ ደቂቃዎች የተሻለ የአሸናፊነት ስነልቦና በመያዛቸው ድሉን ቀድመው እንደጠበቁት ሲናገሩ አጥቂያቸው ሱለይማን ትራኦሬ በቀይ ካርድ በወጣበት ቅፅበት ግብ ጠባቂው አዱኛ ጸጋዬም አብሮ መውጣት እንደነበረበት በመጠቆም የቡድኑ አባላት ሊጉ ላይ ለመቅረት ዕድል እንዳላቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።