ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲዳማ ቡናን 2ለ1 በማሸነፍ ዘንድሮ በሊጉ የነበረውን ተሳትፎ አጠናቋል።
ሲዳማ ቡና ከለገጣፎው ጨዋታ አንፃር በሰባቱ ላይ ለውጥን አድርጓል። አዱኛ ፀጋዬ ፣ ግሩም አሰፋ ፣ መሐሪ መና ፣ ያኩቡ መሐመድ ፣ መኳንንት ካሳ ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ እና በፍቅር ግዛውን በማሳረፍ በፊሊፕ ኦቮኖ ፣ ደግፌ አለሙ ፣ ጊትጋት ኩት ፣ አንተነህ ተስፋዬ ፣ ደስታ ደሙ ፣ ፍሬው ሰለሞን እና እንዳለ ከበደን በቋሚነት ሲያስጀምሩ በፋሲል ሽንፈት ካስተናገደው ስብስባቸው ኤሌክትሪኮች ስንታየሁ ዋለጪን በነፃነት ገብረመድህን ፣ ሔኖክ ገብረህይወትን በፍፁም ገብረማርያም ተክተዋል።
የጨዋታውን የመጀመሪያ አስር ያህል ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሳቸው በይበልጥ ወስደው ለመጫወት አልመው የተንቀሳቀሱት ሲዳማ ቡናዎች ግብ ያስቆጠሩት ገና 9ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ከኤሌክትሪኩ ተከላካይ ተስፋዬ በቀለ እግር ስር እንዳለ ከበደ የነጠቀውን ኳስ የተሻለ አቋቋም ላይ ለነበረው ፊሊፕ አጃህ ሰጥቶት አጥቂው ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ገብቶ ሲዳማን መሪ ያደረገችን ጎል ከመረብ አሳርፏል። የቅብብል ወጥነቶች ባልነበሩበት ቀጣዮቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች በተለይ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች ኳስን በሚይዙበት ወቅት ለሁለቱ የፊት አጥቂዎች በሚሰጧቸው ሰንጣቂ ኳሶች ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረቶች አልተለያቸውም። 11ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ከበደ ከግብ ጠባቂው ካክፓ ሸረፈዲን ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ወደ ጎል ሞክሮ ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና ከግብነት ኳሷን ታድጓታል።
ወደ ጨዋታ እንቅስቃሴ ለመግባት ተቸግረው ረጅሙን ደቂቃ የቆዩት ኤሌክትሪኮች በሒደት የአብዱራህማን ሙባረክን በጥልቀት ወደ ውስጥ እየተሳበ እንዲጫወት ማድረግ ከጀመሩ በኋላ ቡድኑ ቅርፁን የጠበቀ ጥቃቶችን በማድረግ ወደ ጎል በመጠኑም ቢሆንም መቅረብ ችሏል። ሲዳማ ቡናዎች በይገዙ ቦጋለ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው የዕለቱ ሁለተኛ ረዳት ዳኛ ዳንኤል ጥበቡ ከጨዋታ ውጪ የተቆጠረች ግብ ነች በማለት ከሻሩት ከደቂቃዎች በኋላ ኤሌክትሪኮች ባደረጉት ጥራት ያላት ብቸኛ ሙከራቸው የአቻ ግብን በተጋጣሚያቸው መረብ ላይ አሳርፈዋል። ጨዋታው ሊጋመስ 44ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ ከነፃነት መነሻዋን ያደረገችን ኳስ ሙሴ ካቤላ ደርሶት ለአብዱራህማን መሬት ለመሬት ሲያሳልፍለት አጥቂው ቡድኑን 1ለ1 ማድረግ ያስቻለችን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታ ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ መሐል ሜዳ ላይ የነበረባቸውን ድክመት ለማረም የተጫዋች ለውጥን አድርገው የገቡት ኤሌክትሪኮች ወደ መሪነት ያሸጋገረቻቸውን ግብ ወደ ቋታቸው የከተቱት ገና ከጅምሩ ነበር። 47ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ የሲዳማ የሜዳ ክፍል ወደ መስመር ካደላ ቦታ ላይ የተገኘን የቅጣት ምት ጌቱ ሀይለማርያም ሲያሻማ የግብ ጠባቂው ኦቮኖ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት አብዱራህማን ሙባረክ በግንባር ገጭቶ ከመረብ በማሳረፍ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጓታል። ወደ መሪነት ከተሸጋገሩ በኋላ ጥንቃቄን መርጠው ነገር ግን ኳስን በሚያገኙበት ወቅት በፍጥነት በሽግግር ኤሌክትሪኮች ለመጫወት ከሞከሩ በኋላ በተጋጣሚያቸው በእንቅስቃሴ ለመበለጥ ተገደዋል።
ከመሪነት ወደ መመራት መምጣታቸው እያነቃቸው በይበልጥ ጨዋታ ቅኝት ውስጥ የገቡት ሲዳማ ቡናዎች መሐል ሜዳውን ከኮሪደር ተጫዋቾች ጋር በማጣመር የጥቃት መነሻቸውን በማድረግ ቢንቀሳቀሱም ቡድኑ ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ግን ከአጨራረስ አንፃር ደካሞች ነበሩ። በፍሬው ሰለሞን እና ይገዙ ቦጋለ አማካኝነት በእንቅስቃሴ እና ከቆሙ ኳሶች ጎሎችን በማስቆጠር ሲዳማዎች አቻ ለመሆን በመታተር ሲጫወቱ ብንመለከትም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ሳንመለከት ጨዋታው በመጨረሻም ኤሌክትሪክን 2ለ1 አሸናፊ በማድረግ ተቋጭቷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በጨዋታው አጀማመራቸው ጥሩ እንደነበር ተናግረው ሁለተኛ ጎልን ለማስተናገድ ከተገደዱ በኋላ ግን እየወረዱ እንደመጡ ጠቅሰዋል። በጨዋታውም አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማየት እንደሞከሩ ገልፀው ለቀጣይ ዓመት ቡድኑ በበለጠ መደራጀት እንዳለበት ይህም ደረጃ የሚመጥነው እንዳልሆነም ጭምር ጠቁመዋል። የኤሌክትሪኩ አቻቸው ቅጣው ሙሉ በበኩላቸው ድሉ ለሁሉም የቡድኑ አባላት እንዲሆን በማለት ከጀመሩ በኋላ ጨዋታው በጫና ውስጥ ለነበረው ቡድናቸው ጥሩ መነሳሳት ፈጥሮ ማለቁንም ጠቁመዋል።