የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን የቻድ አቻውን በድምር ውጤት 10ለ0 ከረታ በኋላ የቡድኑ አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ተከታዩን የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።
ከባለፈው ጨዋታ አንፃር ዛሬ ተጋጣሚያችን በተሻለ አቀራረብ ነበር የቀረቡት ፤ በእግርኳስ በአንድ ጨዋታ ሁለት ወይም ሶስት ከዛም ከፍ ያለ አቀራረብ ይዘህ ትመጣለህ። የዛሬው ተጋጣሚያችን ግን አንድ ስትራቴጂ ብቻ ነበር ይዞ የገባው ፤ በርካታ የተከላካይ መስመር ተጨዋቾችን ይዘው ስለገቡ የእኛን አጨዋወት ለማበላሸት ሞክረዋል። የእኛ ልጆችም ተከላካይ መስመሩን ለማስከፈት ብዙ ኃይል ጨረሱ። እሱ ነው ጨዋታውን ያከበደብን ፤ ሆኖም ግን ጥሩ ነው 4 ጎል ማግባት ማለት ቀላል አይደለም።
በቀጣይ ልምድ ያላትንና ከባዷን ናይጀሪያን ነው የምትገጥሙት ለእሱ ጨዋታ ተጫዋቾቹን እንዴት ለማዘጋጀት አስበካል…?
እንግዲህ ለቀጣዩ ጨዋታ ሊጉ ይጀምር አይጀምር ገና የታወቀ ነገር የለም። ቢጀምርና ከጨዋታ ቢመጡ ጥሩ ነው የማይጀምር ከሆነ ግን ነገሮች ከባድ ይሆኑብናል። ምክንያቱም ከእረፍት ቀጥታ ለጨዋታው መምጣት ለስራችን አስቸጋሪ ነው። ሆኖም ግን ይሄኛው ቡድን ይቀጥላል ማለት አይደለም ፤ ከ20 አመት በታች ጥሩ ልጆችን አይተናል። እነሱንም ጨምረን ነው ለናይጄሪያው ጨዋታ የምንዘጋጀው። ዝግጅታችን ስናደርግ ለናይጄሪያ የተለየ ዝግጅት አናደርግም ፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያም ከናይጀሪያ የምታስንበት ምንም ምክንያት የለምና።
ከመጀመሪያው ጨዋታ በዛሬው ጨዋታ በተጨዋቾች ቅያሪና የሚና ለውጥን አይተናል። ለዚህ ለውጥ ምክንያትህ ምንድነው?
አዳዲስ ተስፋ ያላቸው ልጆች ለማየት ነው ይሄንን የተጠቀምነው። ለምሳሌ ሎዛን የቦታ ለውጥ እንድታደረግ አድርገናል ፤ ምክንያቱም በቡድኑ ውስጥ መተካካት እንዲኖር ነው። ሎዛ ብቻ ግብ አግቢያችን እንዳትሆን ከሌሎች ልጆችም ግብ እንድናገኝ ነው የሚና ለውጥ ለማድረግ ያሰብነው። በዚህም ተሳክቶልናል ብየ ነው የማስበው ፤ ምክንያቱም ከአዳዲስ ልጆች ጎል አግኝተናልና።