በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነው ሀዋሳ ከተማ ወደ ዝውውሩ በመግባት የሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም የአምስት ነባሮችንም ውል አራዝሟል።
በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ያለፉትን ተከታታይ ሁለት ዓመታት በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ላይ ተቀምጦ የፈፀሙት ሀዋሳ ከተማዎች ለቀጣዩ የ2016 የውድድር ዘመን ከነበሩበት ደረጃ ከፍ ብለው ለማጠናቀቅ የአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረን ውል ከማራዘማቸው በፊት ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን በይፋ ሲያስፈርሙ የአምስት ነባሮችን ውል ማደሱንም ለሶከር ኢትዮጵያ ክለቡ የላከው መረጃ አመላክቷል።
የመጀመሪያ ፈራሚዋ የግብ ዘቧ ቤተልሄም ዮሐንስ ሆናለች። በጌዲኦ ዲላ ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በአርባምንጭ ከተማ ካሳለፈች በኋላ ቀጣዩ መዳረሻዋ ሀዋሳ ሆኗል። ሁለተኛዋ ፈራሚ የመሐል ተከላካዩዋ ትዕግሥት አዳነ ነች። በአርባምንጭ ከተማ በተከታታይ ሦስት ዓመታትን ቆይታ አድርጋ በእግር ኳስ ህይወቷ ሁለተኛ ክለቧን ሀዋሳ አድርጋለች።
የክለቡ ሦስተኛዋ ፈራሚ አማካዩዋ ማዓድን ሣህሉ ነች። ከዳንግላ ከተማ የተገኘችው እና በጥረት ኮርፓሬት ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ከ2014 ጀምሮ በመቻል የነበረችው አማካዩዋ ቀጣይ መዳረሻዋ ሀዋሳ ሆኗል። ሳራ ኪዶ ወደ ቀድሞው ክለቡ በድጋሚ ተመልሳለች። በአማካይ ስፍራ በአርባምንጭ ከተማ ፣ ሀዋሳ እና ለሁለት ዓመታት ደግሞ በመቻል ያሳለፈችው ተጫዋቿ ወደ ቀደመው ክለቧ ዳግም ተመልሳለች።
ፀጋ ንጉሴ የሀዋሳ አምስተኛዋ አዲስ ተጫዋች ሆናለች። በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተጫወተች በኋላ ወደ ቀድሞው ክለቧ መቻል ተመልሳ ዓመቱን ከቋጨች በኋላ ሀዋሳ መዳረሻዋ ሆኗል።
አማካዩ ቤዛዊት ተስፋዬ ወደ ሀዋሳ አምርታለች። በቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኤሌክትሪክ እና ያለፈውን አመት ደግሞ በመቻል ቆይታ አድርጋለች። እፀገነት ግርማ የመጨረሻዋ ፈራሚ ሆናለች። በጌዲኦ ዲላ እና በመቻል ማሳለፍ ችላ ወደ ሀዋሳ አምርታለች።
ክለቡ ከአዳዲሶቹ በተጨማሪ የአምስት ነባር ተጫዋቾችን ውል ለሁለት ተጨማሪ ዓመት አራዝሟል። ግብ ጠባቂዋ መስከረም መንግስቱ ፣ ተከላካዩዋ መንደሪን ክንዲሁን ፣ አማካዩዋ ቅድስት ቴቃ ፣ ተከላካዩዋ ምህረት መለሰ እና አጥቂዋ ቱሪስት ለማ በክለቡ ውላቸው ተራዝሞላቸዋል።
ክለቡ ከላይ ከጠቀስናቸው ፈራሚዎች በተጨማሪ የአዳዲስ ዝውውሮችን መፈፀም እና የነባሮች የማራዘም ስራን በቀጣይ እንደሚሰራ ተጠቁሟል።