ንግድ ባንክ ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

በርካታ ዝውውሮችን የፈፀመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ተገልጿል።
\"\"
ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከስድስት ዓመታት በኋለ መመለሱን ያረጋገጠው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2009 ፈርሶ በ2014 ዳግም ወደ ውድድር በተመለሰ በሁለተኛው ዓመት በሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን ላይ መሳተፍ መቻሉ ይታወሳል። ቡድኑም ለቀጣዩ የውድድር ዘመን የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድን ውል ከማራዘሙ አስቀድሞ ወደ 12 የሚጠጉ አዳዲስ ፈራሚዎችን ወደ ክለቡ ቀላቅሏል። በዚህም ፍሬው ጌታሁን ፣ እንዳለ ዮሐንስ ፣ ፈቱዲን ጀማል ፣ ኪቲካ ጀማ ፣ ፉአድ ፈረጃ ፣ ቢኒያም ጌታቸው ፣ ገናናው ረጋሳ ፣ ሱለይማን ሀሚድ እና ተስፋዬ ታምራትን በይፋ ያስፈረመ ሲሆን የውጪ ዜጋ የሆኑት ካሌብ አማንኩዋ ፣ ባሲሩ ዑመር እና ሲሞይ ፒተር ለማስፈረም ተስማምቶ የአስር ነባር ተጫዋቾችን ውል እንዲሁ ማራዘሙ ይታወቃል። አሁን ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት ከሆነ ክለቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ይፋ ሆኗል።
\"\"
በዚህ መሠረት በአዳማ ከተማ ነገ ዕሁድ ሐምሌ 30 የክለቡ አባላት ከተሰባሰቡ በኋላ ከሰኞ ነሀሴ 1 ጀምሮ ዝግጅት እንደሚጀምሩ ለማወቅ ተችሏል።