ገብረክርስቶስ ቢራራን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠሩት መቻሎች የሁለት ተጫዋቾችን ውል አድሰዋል።
የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በሊጉ ጠንካራ የውድድር ዓመት ማሳለፍ ያልቻሉት መቻሎች ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመሩ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን በሀላፊነት መሾማቸው የሚታወስ ሲሆን ክለቡ ራሱን ለማጠናከር ወደ ዝውውር ከመግባቱ በፊት በክለቡ ውላቸው የተጠናቀቁ ሁለት ተጫዋቾችን ውል በዛሬው ዕለት አድሷል።
ምንተስኖት አዳነ በክለቡ ውሉን ያራዘመው ተጫዋች ሆኗል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድን ከተገኘ በኋላ ለዋናው ክለብ ረጅም ዓመታትን ግልጋሎት የሰጠው በአማካይ እና በተከላካይ ቦታ ላይ የሚጫወተው ምንተስኖት ባለፈው ዓመት አጋማሽ መቻልን ከተቀላቀለ በኋላ በክለቡ በአምበልነትም ጭምር ያገለገለ ሲሆን በክለቡ ለተጨማሪ ዓመት እንደሚቆይም ተረጋግጧል።
ሌላኛው በክለቡ ውሉ የተራዘመለት ተጫዋች የተከላካይ አማካይ በኃይሉ ግርማ ነው። ከዚህ ቀደም በመቻል ከተጫወተ በኋላ በመሐል ወደ ሰበታ አምርቶ የተጫወተው የቀድሞው የሙገር ተጫዋች ሌላኛው በክለቡ መቆየቱ የተረጋገጠው ተጫዋች ነው።
ክለቡ ከሁለቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ በለጠ ወዳጆን ውል ያራዘመ ሲሆን የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውርም በቀጣይ ቀናት እንደሚያገባድድ ይጠበቃል።