የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በፕሪምየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ለማሰልጠን መስማማታቸው ባሳለፍነው ሳምንት ይታወቃል፡፡ በአሰልጣኝ አሸናፊ ቀጣይ የውል ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን አመራሮች ማክሰኞ ጠዋት እንደሚሰበሰቡ ሶከር ኢትዮጵያ ማወቅ ችላለች፡፡
አሰልጣኝ አሸናፊ ዛሬ ከሰዓት የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ስራቸውን በይፋ ይጀምራሉ ተብሎ ቢጠበቅም ከዋልያዎቹ ጋር ያላቸው ቀሪ ውል ባለመጠናቀቁ ይህንን ጉዳይ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ ለመቋጨት ፌዴሬሽኑ ማክሰኞ በሚኖረው ስብሰባ ላይ ይወሰናል፡፡ ብሄራዊ ቡድን በቅርብ አመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አስከፊ ውጤቶችን ያስመዘገበ ሲሆን አሰልጣኙ በግንቦት 2009 ከመጡ በኃላ ማሸነፍ የቻለው ደቡብ ሱዳን እና ጅቡቲን ብቻ ነው፡፡
ዛሬ በኤሌክትሪክ ሜዳ በነበረው የልምምድ ፕሮግራም ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባንክ ተጫዋች ቦጋለ ዘውዴ (ኢንተሎ) አሰልጣኝ አሸናፊ በቀጣዩ ቀናት ያለበትን ወረቀት ስራዎች አጠናቆ ክለቡን እንደሚረከብ ለተጫዋቾች ገለፃ አድርጓል፡፡
እንደታማኝ ምንጮቻችን ከሆነ ፌዴሬሽኑ ከአሰልጣኝ አሸናፊ ጋር ያለው ቀሪ የውል ግዜ የሚያፈርስ ይሆናል፡፡ ይህንን ተክተሎም አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩን ተክተው የቀደሞ የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ በሁለተኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ላይ ቡድኑን እንደሚመሩ ይጠበቃል፡፡