አዲስ አዳጊው ሀምበሪቾ ዱራሜ ተጨማሪ ተጫዋች ሲያስፈርም የወሳኝ የመስመር አጥቂውን ውልም አራዝሟል።
ከቀናት በፊት ወደ ዝውውር መስኮቱ ጎራ በማለት የሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር እና የሁለት ነባሮችን ውል ያራዘመው አዲስ አዳጊው ክለብ ሀምበሪቾ ዱሪሜ በዛሬው ዕለት ደግሞ የአንድ ተጫዋች ዝውውርን ሲቋጭ የወሳኝ የመስመር አጥቂውን በረከት ወንድሙን ኮንትራትም አራዝሟል።
ክለቡን የተቀላቀለው አጥቂው ማናዬ ፋንቱ ነው። የቀድሞው የደቡብ ፓሊስ ፣ መቻል ፣ ኢትዮ ኤልክትሪክ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ሀላባ ፣ ሻሸመኔ እና የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በደሴ ከተማ ተጫውቶ ያሳለፈው አንጋፋው አጥቂ ያለፈውን የውድድር ዘመን በደሴ ከተማ ጥሩ ቆይታ ማድረጉን ተከትሎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰበትን ዝውውር አጠናቋል።
በክለቡ ውሉ የታደሰለት ተጫዋች የመስመር አጥቂው በረከት ወንድሙ ነው። ከወላይታ ድቻ ወጣት ቡድን የተገኘው ተጫዋቹ ለሀምበሪቾ ዱራሜ ወደ ሊጉ ማደግ በከፍተኛ ሊግ ቆይታው 8 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በክለቡ ውሉን በዛሬው ዕለት አድሷል።