በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ሀገራችንን የሚወክሉት ባህር ዳር ከተማዎች ለቀናት ልምምዳቸውን ካቆሙ በኋላ ዳግም ነገ ወደ ልምምድ ይመለሳሉ።
በአሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወቃል። ደረጃውን ተከትሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር የሚሳተፈው ክለቡ በዝውውር መስኮቱ ራሱን ካጠናከረ በኋላ ሐምሌ 23 በመቀመጫ ከተማው ልምምድ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም አራት ቀናት ብቻ ልምምዱን አከናውኖ በክልሉ በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ልምምዱን መቀጠል አልቻለም ነበር።
ግማሾቹ የቡድን አባላት ከቀናት በፊት ወደ መዲናችን አዲስ አበባ መጥተው የነበረ ሲሆን ቀሪዎቹ ተጫዋቾች እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላት በዛሬው ዕለት ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ ታውቋል። ማረፊያውን በሳሬም ሆቴል ያደረገው ክለቡ የዛሬ ሳምንት ዕሁድ ከአዛም ጋር ላለበት ወሳኝ መርሐ-ግብርም አዲስ አበባ ላይ በነገው ዕለት ልምምዱን ለመጀመር ያቀደ ሲሆን ይህንን ዘገባ እያጠናከርን እስካለንበት ጊዜ ድረስ የልምምድ ሜዳ የመፈለግ ስራ እየተሰራ እንደሆነ አውቀናል።