የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወደ አዲስ አበባ ሊመለስ ነው

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ሊጉ በቀጣይ ዓመት ወደ መዲናችን መቼ እንደሚመለስ ተናገሩ።

በአሁኑ ሰዓት በየ2015 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ፕሮግራም እና የኮከቦች ሽልማት መርሐ-ግብር በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል እየተከናወነ ይገኛል። የመክፈቻ ንግግር እያደረጉ የሚገኙት የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የ2015 የውድድር ዓመት በጥሩ ሁኔታ በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው በዓመቱ ተፈጠሩ ያሏቸውን ተግዳሮቶች መግለፅ ይዘዋል። በዚህም የውድድር መርሐ-ግብሮች መቆራረጥ ዋነኛው ችግር እንደሆነ ገልፀዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ከአስገዳጅ ምክንያቶች ውስጥ የሜዳ ችግር እንደሆነ አመላክተው በንግግራቸው መካከል ሊጉ ወደ መዲናችን አዲስ አበባ መች እንደሚመለስ ተናግረዋል።

በዚህም ከሦስት ዓመታት በኋላ የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዓመት ከገና በዓል በኋላ (ከታኅሣሥ መጨረሻ በኋላ) በመዲናችን አዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚደረግ ይፋ አድርገዋል።