ወልቂጤ ከተማ አማካይ ሲያስፈርም የአንድ ተጫዋች ውል አራዝሟል

በሀዋሳ የቅድመ ውድድር ዝግጅት የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች የተከላካይ አማካይ ሲያስፈርሙ የመስመር አጥቂውን ውል አድሰዋል።

በአዲሱ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እየተመሩ በሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በማጣመር እየሰሩ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች በክረምቱ የዝውውር መስኮት እስከ አሁን አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረሙ ሲሆን አሁን ደግሞ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነውን ዳንኤል መቀጮን አስራ ሦስተኛው አዲስ ፈራሚ ተጫዋች በማድረግ ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።

ዳንኤል የቀድሞው የደቡብ ፓሊስ እንዲሁም የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ደግሞ በንብ ሲጫወት ከቆየ በኋላ አዲሱ የወልቂጤ ፈራሚ ሆኗል።

ክለቡ ከአዲስ ፈራሚው በተጨማሪ የቀድሞው የሲዳማ ቡና የተጠናቀቀውን ዓመት በበኩሉ በወልቂጤ ቆይታ የነበረውን የመስመር አጥቂው ተመስገን በጅሮንድን ውል ለተጨማሪ ዓመት አድሷል።