ከ10 ዓመታት በላይ ከሀገር ውጪ ሲጫወት የነበረው ሽመልስ በቀለ ወደ ሀገር ውስጥ ተመልሶ መቻልን ተቀላቅሏል።
በአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመራው መቻል በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ክፍተት በነበረበት ቦታ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማምጣት እንዲሁም ውላቸው ከተጠናቀቀ ተጫዋቾች መካከል የሶስቱን በማራዘም የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በቢሾፍቱ ከተማ እያከናወነ ይገኛል። ክለቡም በዝውውር መስኮቱ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ሲጥር እንደነበረ ሲሰማ የነበረ ሲሆን የአንደኛውን ዝውውርም ከደቂቃዎች በፊት በይፋ ፈፅሟል።
ክለቡን የተቀላቀለው ተጫዋች ሽመልስ በቀለ ነው። ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ፔትሮጀትን በመቀላቀል የግብፅን እግርኳስ የተዋወቀው ሽመልስ በቀለ በክለቡ ለስድስት ዓመታት ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ ሌላኛውን የሀገሪቱ ክለብ ምስር ለል መቃሳን ተቀላቅሎ የነበረ ሲሆን ከ2 ዓመታት በፊት በመቃሳ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ቢኖረውም በስምምነት ተለያይቶ የኤል ጎውናን መለያ በመልበስ በሊጉ ሲጫወት ነበር። ተጫዋቹ ከ ኤል ጎውና በኋላም ዑመድ ኡኩሪ ተጫውቶበት የነበረውን ኤንፒ በሁለት ዓመት ውል ተቀላቅሎ የነበረ ሲሆን ቀሪ አንድ ዓመት እያለው ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያይቶ ዳግም ወደ ሀገሩ ተመልሷል።
ከግብፅ በፊት በሱዳን ሊግ ተጫውቶ የነበረው የወቅቱ የዋልያዎቹ አምበል ሽመልስ ከሀገር ከመውጣቱ በፊት በሀዋሳ ከተማ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታ ማድረጉ አይዘነጋም። ተጫዋቹም በመቻል ለሁለት ዓመት ግልጋሎት ለመስጠት ፊርማውን ማኖሩን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።