ሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ | መቻል እና ሲዳማ ቡና የፍፃሜ ተፋላሚ ሆነዋል

የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ተደርገው መቻል እና ሲዳማ ቡና የዋንጫ ተጋጣሚ መሆናቸውን አውቀዋል።

በሀዋሳ እየተደረገ የሚገኘው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ተጠናቀው የግማሽ ፍፃሜ መርሀግብር ዛሬ ሲደረግ መቻል ወላይታ ድቻን ፣ ሲዳማ ቡና በጎሎች ታጅቦ ሀዋሳ ከተማን በመርታት የፍፃሜ ተፈላሚ መሆናቸው ታውቋል። 07፡00 ሲል መቻልን ከወላይታ ድቻ አስተናግዶ የነበረው ቀዳሚው ጨዋታ መቻልን ወደ ፍፃሜ ያሳለፈ ውጤት ተመዝግቦበታል። ተመጣጣኝ ፉክክርን ነገር ግን ከሙከራዎች አኳያ ደብዛዛ እንቅስቃሴ ያስተዋልንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ከነዓን እና ሙሀባ በመቻል በኩል ካደረጉት ሙከራ ውጪ የጎሉ ነገሮችን አላስተዋልንበትም።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል መቻሎች በሁሉም ረገድ በተሻለ የተንቀሳቀሱበት ነበር። 76ኛው ደቂቃ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ ዮዳሄ ዳዊት ማራኪ ግብን አስቆጥሮ መቻልን መሪ አድርጓል። የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው በማድረግ ይበልጥ ብልጫን በመውሰድ ይጫወቱ የነበሩት መቻሎች በወጣቱ አማካይ ዮሐንስ መንግሥቱ ተጨማሪ ግብን በማስቆጠር 2-0 አሸንፈው ወጥተዋል።

በመቀጠል ሀዋሳ ከተማን ከሲዳማ ቡና ያገናኘው መርሀግብር ሲዳማ ቡና በጎል ተንበሽብሾ ሀዋሳን 5ለ1 ረቷል። ጨዋታው 11ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ይገዙ ቦጋለ ከመሐል ክፍሉ የደረሰውን ኳስ የተከላካዮች እና የግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋንጎ የጊዜ አጠባበቅ ክፍተትን ተመልክቶ ጎል አስቆጥሯል። ተጫዋቹ ከግቧ በኋላ ጠንከር ያለ ጉዳት አስናግዶ ከሜዳ ወጥቷል። ጨዋታው ቀጥሎ በተሻለ መነቃቃት ውስጥ የሚገኙት ሲዳማዎች 24ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተገኘን ኳስ ይስሀቅ ሲያመቻችለት ብርሀኑ በቀለ የቀድሞው ክለቡ ላይ ተጨማሪ ግብ አክሏል።

 

ሁለተኛ ጎልን ለማስተናገድ የተገደዱት ሀዋሳዎች ተከላካዩ ሚሊዮን ሠለሞን ከዕለቱ ዳኛ ጋር በፈጠረው ግብ ግብ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲመለስ ሀዋሳዎች ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸው ግብ በበረከት ሳሙኤል የግንባር ግብ ቢያገኙም የኋላ ኋላ ሲዳማዎች በፈጠሩት ወጥ የሆነው የማጥቃት ባህሪ ይስሀቅ ካኖ ፣ ዳመነ ደምሴ እና ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ ላይ በቡልቻ ሹራ አማካኝነት ግቦችን አግኝተው ጨዋታው በሲዳማ ቡና 5ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

የፊታችን ሰኞ መስከረም 14 ለደረጃ ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ ለፍፃሜ ሲዳማ ቡና ከመቻል በሚያደርጉት መርሀግብር ውድድሩ ይደመደማል።