ሉሲዎቹ ከ 2024 የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ውጪ ሆነዋል

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሉሲዎቹ በመለያ ምቶች በብሩንዲ አቻቸው ተሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር ሳያልፉ ቀርተዋል።

ለ 2024 የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የአንደኛ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ 1-1 የተለያዩት ኢትዮጵያ እና ብሩንዲ የመልስ ጨዋታቸውን እንደመጀመሪያው ጨዋታ ሁሉ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲያደርጉ ቀን 9፡30 ሲል በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን በቁጥር በዝቶ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ሙሉ ብልጫውን የወሰዱት ሉሲዎቹ 4ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት ከተገኘ የቅጣት ምት በንቦኝ የን አማካኝነት የመጀመሪያ ሙከራቸውን ሲያደርጉ 10ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሎዛ አበራ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሯ አክርራ የመታችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ አስወጥታባታለች።


ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ በሚቆራረጡ ኳሶች ይታጀቡ እንጂ በጠንካራ እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቀላሉ መድረስ የቻሉት ኢትዮጵያዊያን 19ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ረድዔት አስረሳኸኝ ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት የመታችው ኳስ በግብ ጠባቂዋ አሚሳ ኢናሩኩንዶ እጅግ የወረደ ብቃት በእግሯ መሃል አልፎ ግብ ሆኖ ተቆጥሯል።

ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን ለመድረስ እጅግ የተቸገሩት ብሩንዲዎች 24ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ካንያሙኔዛ ኤሪካ በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረችው እና አኔላ ኡዊማና በግንባሯ የገጨችው ኳስ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቷል።


ከዕረፍት መልስ ብሩንዲዎች ባልተጠበቀ የማጥቃት እንቅስቃሴ በሳንድሪን ኒዮንኩሩ አማካኝነት የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ሆኖም አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የተከላካይ መስመር ተጫዋች ቀንሶ አጥቂ በመጨመር እና አሰላለፉን በመቀየር በርካታ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክርም ተጫዋቾቹ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በተለይም 54ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ ሆና የቀነሰችውን ኳስ ያገኘችው ረድዔት አስረሳኸኝ ሳትጠቀምበት ቀርታ ትልቅ የግብ ዕድል ስታባክን በአምስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ሎዛ አበራ በቄንጥ ያቀበለቻትን ኳስ ያገኘችው አርያት ኦዶንግ በደካማ አጨራረስ አባክናዋለች።

በቁጥር በመብዛት ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን ለመድረስ ሲሞክሩ የነበሩት ሉሲዎቹ 68ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። አረጋሽ ካልሳ በጥሩ ዕይታ ለአርያት ኦዶንግ የሰነጠቀችውን ኳስ አጥቂዋ እጅግ በዘገየ ሩጫ እና በደካማ አጨራረስ ሁለተኛ ወርቃማ ዕድሏን ስታባክን 78ኛው ደቂቃ ላይም የብሩንዲ ተከላካዮች በተዘናጉበት ቅጽበት ግልጽ የማግባት ዕድል ያገኘችው ረድዔት አስረሳኝ እንደ አርያት ሁሉ ሁለተኛ የማስቆጠር አጋጣሚዋን ባልተረጋጋ እና ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ሆኖም ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሄዶ 1-1 ተጠናቋል። የደርሶ መልስ ውጤቱ 2-2 በመሆኑም በተሰጡ የመለያ ምቶች ብሩንዲ 5ለ3 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን ስታረጋግጥ በሁለተኛ ዙር ማጣሪያም ምሽት ላይ በሚደረገው የአልጀሪያ እና ዩጋንዳ አሸናፊ ጋር የምትጫወት ይሆናል።