የዓለም ዋንጫ ከሃያ ዓመታት ቆይታ በኋላ በአፍሪካ ምድር ለመካሄድ ተቃርቧል።
ሞሮኮ ፣ ፖርቹጋል እና ስፔን የ2030 የአለም ዋንጫ የማዘጋጀቱን ዕድል እንደተሰጡ በርካታ ታማኝ ዓለም አቀፍ ሚድያዎች እየዘገቡት ይገኛሉ። ምንም እንኳ ሦስቱ ሀገራት ውድድሩን ለማዘጋጀት ዕድል ቢሰጣቸውም ፊፋ ባልተለመደ መልኩ ኡራጓይ ፣ አርጀንቲና እና ፓራጓይ የመክፈቻ ሶስት ጨዋታዎችን እንዲያስተናግዱ ዕድል ሰጥቷቸዋል። ይህንን ተከትሎም ውድድሩ ለመጀመርያ ግዜ በሦስት አህጉሮች የሚካሄድ ይሆናል።
ውሳኔው ረቡዕ በበይነ መረብ በተካሄደው የፊፋ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተወሰነ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት የመጨረሻ ወራት 211 የፊፋ አባላት በሚሰጡት ድምጽ ይፋዊ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ውሳኔም ዩኤፋ እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት የተገኘ ሲሆን ቀደም ብለው ዩክሬንን የዝግጅቱ አካል የማድረግ እቅድ እንደነበራቸውም ተገልጿል።