ኢትዮጵያ ቡና እስከቀጣዩ ወር አጋማሽ ድረስ በጉዳት ላይ የሚገኙ አምስት ተጫዋቾቹን ግልጋሎት እንደሚያገኝ ተገልጿል።
በአዲሱ ሰርብያዊ አሰልጣኝ ካቫዞቪች ኒኮላ እየተመሩ የመጀመርያ የሊግ ጨዋታቸውን ያሸነፉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ለረዥም ጊዜ ከሜዳ የራቁ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው መልሰው ለማግኘት መቃረባቸውን ገልፀዋል።
ክለቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በተለያዩ ምክንያቶች ከቡድኑ ጋር ልምምድ ያላደረገው አምበሉ አማኑኤል ዮሐንስ መስከረም 29 የልምምድ ዝግጅቱን አጠናቆ ቡድኑን ይቀላቀላል። በተመሳሳይ ሌላው አማካይ አብዱልሐቪዝ ቶፊቅ ደግሞ መስከረም 27 ቡድኑን ይቀላቀላል ተብሎ ሲጠበቅ መሐመድኑር ናስር ከሦስት ሳምንታት በኋላ ጥቅምት 14 ወደ ቡድኑ እንደሚመለስ ይጠበቃል። ሦስቱ ተጫዋቾች በተመሳሳይ የተያዘላቸውን የልምምድ ጊዜ ካጠናቀቁ በኋላ ለውድድር ብቁ ሆነው ቡድኑን የሚቀላቀሉ ይሆናል።
በተመሳሳይ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቀው የነበሩት ተከላካዩ ራምኬል ጀምስ እና ሬድዋን ናስር ከጉዳት ተመልሰው ከቡድኑ ጋር መጠነኛ ልምምድ ማድረግ መጀመራቸው ሲታወቅ ከሲዳማ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ግብ ጠባቂው በረከት አማረም በነገው ዕለት ወደ ልምምድ እንደሚመለስ ታውቋል።
በወንጂ ስታዲየም መደበኛ ልምምዳቸው በማድረግ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በቀጣይ ድሬዳዋ ከተማን ይገጥማሉ።