ስድስት ግቦች በተቆጠሩበት እና ማራኪ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ ኃይቆቹ እና ዐፄዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል።
በሁለቱም ቡድኖች በኩል ሳቢ እንቅስቃሴዎች ባልታዩበት የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ሁኔታ በመረጋጋት ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የተቸገሩበት ነበር።
የኋላ ኋላ ግን ዐፄዎቹ በተሻለ መንገድ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ያገኟቸውን ዕድሎች ወደ ግብነት በመቀየር ጨዋታውን መምራት ችለዋል። በ9ኛው ደቂቃም ሱራፌል ዳኛቸው በሀዋሳ ሳጥን አካባቢ የተገኘችውን ቅጣት ምት ግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ ያሻማዋል ብሎ በተዘናጋበት ቅፅበት በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
በአጋማሹ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ቅርፅ እና የማጥቃት ደመነፍስ የነበራቸው ፋሲሎች በ20ኛው ደቂቃም በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። አጥቂው ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ያሻገራትን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ነበር የቡድኑ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ያደረገው። በጨዋታው የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ያልቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በአጋማሹ የመጨረሻ ጥቂት ደቂቃዎች በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ታፈሰ ሰለሞን አሻምቶት ሙጂብ ቃሲም በግንባር ገጭቶ ካደረገው ሙከራ ውጭ ተጠቃሽ የጠራ ዕድል መፍጠር አልቻሉም።
ከመጀመርያው አጋማሽ የተለየ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ የአጨዋወት ለውጥ አድርገው የተመለሱት ሀዋሳ ከተማዎች ተሻሽለው የቀረቡበት ነበር። ይህንን ተከትሎም በአጋማሹ የመጀመርያ ደቂቃ ላይ በታፈሰ ሰለሞን አማካኝነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። አማካዩ ሀዋሳ ከተማዎች የከፈቱትን ጥቃት ተከትሎ ከፋሲል ግብ ክልል የተመለሰን ኳስ በመምታት ነበር ያስቆጠረው።
በአጋማሹ በጥሩ መነቃቃት የተመለሱት ሀዋሳዎች 55ኛው ደቂቃ ላይም የፋሲል ተከላካዮችን የትኩረት ማጣት እና የመናበብ ክፍተት ተጠቅመው በዓሊ ሱሌማን አማካኝነት ግብ በማስቆጠር አቻ መሆን ችለዋል። ፈጣኑ አጥቂ ከመሀል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ ከተከላካዮች ጀርባ ሮጦ ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ በመምታት ነበር ግቡን ያስቆጠረው።
ጨዋታው አቻ ከሆነ በኋላ ፋሲሎች ኳሱን በመያዝ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ሀዋሳዎች በበኩላቸው በፈጣን የመስመር የመልሶ ማጥቃቶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ሁለቱ ቡድኖች ለግብ የቀረቡ የጠሩ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። በዐፄዎቹ በኩል መናፍ ከቆመ ኳስ የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራም ከታዩ ሙከራዎች የተሻለው ለግብ የቀረበ ነበር።
ኃይል በተቀላቀለባቸው አጨዋወቶች ታጅቦ በቀጠለው ጨዋታ 80ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች ግብ አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል። በረከት ሳሙኤል ተቀይሮ ገብቶ ጨዋታ ቀያሪ እንቅስቃሴ ያደረገው ዐሊ ሱሌማን ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ በማስቆጠር ሀዋሳዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ከቆመ ኳስ ዐፄዎቹን መሪ ያደረገች ግብ ያስቆጠረው ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥኑ ጠርዝ አካባቢ ያገኛትን የቆመች ኳስ በድጋሚ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩትም የሀዋሳው ተከላካይ በረከት ሳሙኤል በተከታታይ ባያቸው ሁለት ቢጫዎች በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
ስድስት ግቦችና ጠንካራ ፉክክር ያስመለከተን የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ አስቀድመው ሀሳባቸውን የሰጡት የሀዋሳው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በመጀመርያው አጋማሽ ብልጫ እንደተወሰደባቸው ገልፀው ግብ ጠባቂያቸው ረጅም ጊዜ ከጨዋታ ርቆ ስለቆየ የትኩረት ችግር እንደነበረበት ጠቅሰዋል። አሰልጣኙ አክለውም በሁለተኛው አጋማሽ የአጨዋወት ለውጥ አድርገው መግባታቸውን እና ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ በጥሩ መነሳሳት መጫወቱ ጥሩ እንዲንቀሳቀሱ እንደረዳቸው ተናግረዋል። ቀጥለው ሀሳባቸውን የሰጡት የፋሲሉ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው ቡድናቸው የመጀመርያውን አጋማሽ በጥሩ መንገድ እንደጀመረ ጠቅሰው በአጋማሹ በርካታ ዕድሎች እንዳመከኑ ተናግረዋል። ከዕረፍት በኋላ ጥሩ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ እና የተከላካይ መስመሩ ላይ አለመናበብ እንደነበርም ጠቅሰዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም በጨዋታው በርካታ ዕድሎች ቢያመክኑም ነጥብ መጋራታቸው መጥፎ እንዳልሆነ ተናግረዋል።