የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ነገ ይከናወናሉ። እኛም አራቱን ክለቦች የተመለከቱ የቅድመ ውድድር ዝግጅት እና መሰል ጉዳዮችን በተከታይ ፅሑፋችን አንስተናል።
የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደቀጠለ ነው። የአንደኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ሲደረጉ ቆይተው በነገው ዕለት በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይገባደዳሉ። እኛም በዚህ ፅሑፋችን ወልቂጤ ከተማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ባህርዳር ከተማ ስለ ነበራቸው የዝግጅት ምዕራፍ እንመለከታለን።
ወልቂጤ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
– የ2015 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ጊዜን በውስብስብ ፈተናዎች ውስጥ ሆነው ካጠናቀቁ ክለቦች መካከል ወልቂጤ ከተማን በግንባር ቀደምነት መጥቀስ ይቻላል። በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ አጋፋሪነት የውድድር ዘመኑን ሲመራ የነበረው ቡድኑ በሜዳ ላይ ወጥ ካልሆነው አቋሙ ውጪ ያሉ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በእጅጉ እንዲፈተን አድርገውት እንደነበር ይታወሳል። በእነኚህ ሁሉ ጉዞዎች ውስጥ ያለፈው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ የሊግ ጨዋታዎች በተለይ ከሦስቱ ላይ ያገኛቸው ነጥቦች አግዘውት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ35 ነጥቦች 13ኛ ላይ በመቀመጥ ለከርሞ እንዲሰነብት ሆኖ ዓመቱ ተገባዷል። ለዘንድሮው የውድድር ዘመን የአስተዳደር መዋቅሩን በዞን ደረጃ ከፍ አድርጎ በመቀጠል ወደ አሰልጣኝ ቅጥር ገብቶ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን ጨምሮ ሌሎች ረዳቶችን የቀጠረ ሲሆን ዘግየት ብሎም ቢሆን በተሳተፈበት ዝውውር በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል። ቡድኑ ጥገኛ የማጥቃት አማራጩ የሆነውን ጌታነህ ከበደን ጨምሮ እንደ ብዙዓየሁ ሰይፈ እና መሰል ወሳኝ ተጫዋቾችን ቢያጣም ምትክ ሊሆኑ የሚችሉትን ደግሞ በየቦታው አስፈርሟል። እንደ መሳይ አያኖ ፣ መሳይ ፓውሎስ ፣ ሔኖክ ኢሳያስ ፣ ዳንኤል መቀጮ ፣ ሙሉዓለም መስፍን ፣ ጄይላን ከማል ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ አሜ መሐመድ ፣ ዳንኤል ደምሱ ፣ ጌቱ ኃይለማርያም ፣ በቃሉ ገነነ ፣ ራምኬል ሎክ ፣ ጋዲሳ መብራቴ ፣ መሐመድ ናስር እና ወንድማገኝ ማዕረግን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ በመቀላቀል በክለቡ ከነበሩ ጥቂት ተጫዋቾች ጋር በማቀናጀት ወደ ቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ በማስከተል ገብተዋል። በሀዋሳ ከነሐሴ 20 ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ የሰነበቱት ሠራተኞቹ በዝግጅታቸው ወቅት በይበልጥ ራሳቸውን ለመፈተሽ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ተሳትፎን አድርገው ነበር። በውድድሩ ወቅት በምድብ መርሐ-ግብሮቻቸው ውጤታማ ጊዜን ማሳለፍ ባይችሉም በጨዋታ ሒደት ወደ መስመር ባዘነበለ መልከ ለመጫወት ሲሞክሩ የሚታይ ቅርፅ እንዳላቸው ተመላክቷል። ይሁን እንጂ ቡድኑ ለተጋጣሚ ቡድኖች ይሰጠው የነበረውን ነፃ የመጫወቻ ሜዳ የመፍቀድ ባሕሪን በነገው የመጀመሪያ ጨዋታው ላይ ካስመለከተን የተለየ ውጤትን ልንመለከት እንደምንችል መገመት ይቻላል።
– የሊጉን ዋንጫ በተከታታይ ሁለት ዓመታት ያሳካው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮም ሌላኛውን የድል ጉዞ እያሰበ እንደሚመጣ የሚጠበቅ ቢሆንም በክለቡ ያሉ ወሳኝ ተጫዋቾችን ማጣቱ ደግሞ ሌላ ስጋትን ይዞ ሊመጣ ይችላል የሚሉ ጉዳዮች ተነስተዋል። በ64 ነጥቦች ሊጉን በበላይነት አጠናቅቆ የዋንጫ ድሉን ዓምናም ያሳካው ቡድኑ ከሌሎች ክለቦች ቀደም በማለት በአፍሪካ መድረክ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ መሆኑን ተከትሎ ዝግጅቱን ማድረግ የጀመረው ገና በጊዜ ነበር። ነሐሴ 24 በቢሾፍቱ በሚገኘው የይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ውስጥ በነባር ተጫዋቾቹ ዝግጅቱ የጀመረው ቡድኑ በሒደት ወደ ዝውውሩ ገብቶ በመጠኑም ቢሆን ራሱን ጠግኗል። በክለቡ ውስጥ በተከታታይ ዓመታት በስኬቱ ወቅት ካሉት መካከል በአሰልጣኝ ቡድን አባላት መካከል እንደ አዲስ ወርቁን በተጫዋች ደረጃ ቻርለስ ሉክዋንጎ ፣ ሱለይማን ሀሚድ ፣ አዲስ ግደይ ፣ ሀይደር ሸረፋ ፣ ጋቶች ፓኖም ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል ፣ ቸርነት ጉግሳ እና ወሳኙን አጥቂ እስማኤል ኦሮ አጎሮን ያጣ ሲሆን እነርሱን ለመተካትም ደግሞ በቀጥታም ሆነ በሙከራ አዳዲስ ተጫዋቾችን ቀላቅሏል። ፋሲል ገብረሚካኤል ፣ አዲሱ ቦቄ ፣ አማኑኤል አረቦ ፣ አማኑኤል እንዳለን ከሀገር ውጪ ደግሞ እንደ ሞሰስ ኦዶ እና ክዋሜ ፍሪምፓንግ አይነት ተጫዋቾችንም አግኝቷል። ምንም እንኳን ቡድኑን በይፋ እስከ አሁን መቀላቀል ያልቻሉት አሸናፊ ፊዳ እና እንዳልካቸው መስፍንም በስብስቡ ውስጥ ተካተዋል። በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ መሪነት በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ላይ ከዛንዚባሩ ኬኤም ኬኤም ጋር በመደልደል በጊዜ ወደ ውድድር የገባው ቡድኑ በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታው ድልን ቢያገኝም በሁለተኛው ዙር በግብፁ አልአሀሊ በደርሶ መልስ ውጤት ተረቶ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል። ክለቡ በአራቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች ወቅት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በተለይ ከመስመር መነሻቸው ካደረጉ ኳሶች ጥቃቶችን ለማግኘት ሲሞክር መመልከት ብንችልም ከአጨራረስ አንፃር ጥድፊያዎች መታየታቸው በነገው የሊግ መርሐ-ግብራቸው ይሄንኑ የሚደግሙት ከሆነ ከውጤት አንፃር ተቃራኒ ነገሮች ሊገጥሟቸውም ይችላሉ። ነገር ግን እነኚህን ችግሮች አጥብቦ አቀራረባቸውን ልክ እንደ ተለመደው የሚያደርጉ ከሆነ ከጨዋታው ሦስት ነጥብን ሊያገኙ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ መድን ከ ባህርዳር ከተማ
– ወደ ሊጉ ዳግም ከተመለሰ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው ኢትዮጵያ መድን ዘንድሮም ለሌላኛው የውድድር ፈተና ራሱን አዘጋጅቷል። በአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ እየተመራ የ2015 የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎውን ማድረግ የጀመረው ክለቡ በመጀመሪያው የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ካስተናገደው አስከፊ ሽንፈት በኋላ ባሉት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ያስመዘገባቸው ውጤቶች ረድተውት በመጣበት ዓመት ለዋንጫ ባለቤትነት ሽሚያ ራሱን ሲያሳትፍ ቆይቶ በመጨረሻም 3ኛ ደረጃን በመያዝ ሊጉን ማጠናቀቁ ይታወሳል። ከዓምናው የቡድኑ ስብስብ አኳያ ልዩነት ሲፈጥሩ በሜዳ ላይ ያስተዋልናቸውን ጋናዊያኑን ሐቢብ መሐመድ እና ባሲሩ ዑመር ፣ ዩጋንዳዊውን ሲሞን ፒተርን ጨምሮ ኪቲካ ጀማ እና ቴዎድሮስ በቀለን እንዲሁም ወሳኝ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለሌሎች ክለቦች አሳልፎ የሰጠ ሲሆን በእነርሱ ምትክ ደግሞ እንደ ተመስገን ዮሐንስ ፣ ንጋቱ ገብረሥላሴ ፣ አዲስ ተስፋዬ ፣ አቡበከር ወንድሙ ፣ ማታይ ሉል ፣ መሐመድ አበራ ፣ ሙሴ ከበላን እና ናይጄሪያዊውን ኦቤና አቤኔዘርን በመቀላቀል ከነሐሴ 7 ጀምሮ አዳዲሶቹን እና ነባሮችን በማቀፍ በአዳማ የዝግጅት ጊዜውን በማሳለፍ ቆይታ አድርጓል። ቡድኑ ያለፈውን ዓመት በተለይ በአማካይ እና በመስመር በኩል ጥሩ አጨዋወትን በመጫወት ከተጋጣሚው ነጥቦች ሲያገኝ ያየን ቢሆንም በዓምናው ስብስቡ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋቾች ዘንድሮ አለመኖራቸው አንዳች ነገር ቡድኑ ላይ ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል። ይሁን እንጂ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ካላቸው ልምድ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ከራስ ሜዳ ኳሶችን በመጀመር ተጋጣሚ ሜዳ ላይ በፍጥነት ለመገኘት የሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ በሆነ መንገድ ካስቀጠሉ ግን ቡድኑ ልዩነት ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ይመስላል።
– የጣና ሞገዶቹ ዘንድሮ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሳተፉበት የአፍሪካ መድረክ ላይ ራሳቸውን በተሻለ ለማዘጋጀት በማሰብ ነበር የዝግጅት ጊዜያቸውን ቀደም ብለው ማከናወን የጀመሩት። በፕሪምየር ሊጉ ያለፈውን ዓመት በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው መሪነት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት ባህርዳር ከተማዎች ሳይጠበቅ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳዩ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማሳካት እስከ መጨረሻዎቹ ሳምንታት ተጉዘው የውድድር ዓመቱን በ 60 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ማጠናቀቅ መቻላቸው ይታወሳል። ሊጉን ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ማጠናቀቃቸውን ተንተርሶ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ሀገራችንን ወክለው የነበሩት ባህርዳሮች ከታንዛኒያው አዛም ጋር በቅድመ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ መደልደላቸውን ተከትሎ በጥቂት ዝውውሮች ላይ በመሳተፍ ቡድናቸው መገንባት ጀምረዋል። እንደ አለልኝ አዘነ እና መሳይ አገኘሁ ሁነኛ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው አካተው በማስከል ወደ ገበያው የወጡት የጣና ሞገዶቹ ከሀገር ውጪ ግብ ጠባቂው ፔፕ ሰይዶን ፣ አብዱላዚዝ ሲሆኔን እና ሱለይማን ትራኦሬን ከሀገር ውስጥ ደግሞ ፍሬው ሠለሞን ፣ ፍሬዘር ካሳ ፣ ቸርነት ጉግሳ ፣ አባይነህ ፊኖ እና ረጀብ ሚፍታህን ከከፍተኛ ሊጉ በማካተት ከሐምሌ 24 ጀምረው ባህርዳር ላይ ዝግጅታቸውን ጀምረዋል። ቡድኑ በባህርዳር ቆይታው ጥቂት ልምምድን ብቻ ካደረገ በኋላ በአካባቢው ከነበረው አለመረጋጋት አንፃር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ዝግጅትን የቀጠለው ቡድኑ በማስከተል ወደ ማጣሪያ ጨዋታዎቹ ገብተው አዛምን በደርሶ መልስ አሸንፈው ወደ ሁለተኛው ዙር በማለፍ ጠንካራ ተሳታፊ ሆነው ብናያቸውም ፣ በሁለተኛው የማጣሪያ መርሐ-ግብራቸው የቱኒዚያውን ክለብ አፍሪካን አዲስ አበባ ላይ ጋብዘው 2ለ0 አሸንፈው የነበረ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር ግን ቱኒዚያ ላይ 3ለ0 ተሸንፈው በድምር ውጤት ተረተው ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል። ቡድኑ በእነኚህ የማጣሪያ ጨዋታዎቹ ወቅት ተጋጣሚ መረብ ላይ ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ውጤትን ሲይዝ ያየን ቢሆንም የኋላ ክፍሉ በቀላሉ የሚሰራቸው የጊዜ አጠባበቅ ስህተቶች ዋጋ እንዳስከፈሉትም በግልፅ ተንፀባርቋል። ምናልባትም ቡድኑ ነገ የተጠቀሱትን ክፍተቶች ደፍኖ ከቀረበ ደግሞ ያለ አንዳች ጥርጥር ካለው የቡድኑ መዋቅራዊ አቅም አንፃር ውጤታማ መሆን እንደሚችል በልበ ሙሉነት መናገር ያስችላል።