በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚጫወቱ ሦስት የውጪ ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎላቸዋል።
ቀደም ብሎ አሰልጣኝ ሰርጅዮቪች ሚሎቲን ሚቾን ያሰናበተው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን በጊዜያዊ አሰልጣኙ ሞርሌይ ብዬክዋሶ እየተመራ ከማሊ እና ዛምቢያ ጋር ለሚያደርጋቸው ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች 36 ተጫዋቾችን ያካተተውን ጊዜያዊ ስብስብ ይፋ ሲያደርጉ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የሚጫወቱ ሦስት ተጫዋቾችን አካቷል።
በቡድኑ ከተካተቱት ተጫዋቾች መካከል የመጀመርያው በቅርቡ መቻልን የተቀላቀለው ናፍያን አልዮንዚ ነው። ለዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ስድስት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ የተጫወተው ይህ የ27 ዓመት ግብ ጠባቂ ለሦስተኛ ጊዜ ሀገሩን እንዲያገለግል ጥሪ ደርሶታል።
ሁለተኛው ጥሪ የደረሰው ተጫዋች ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ ያሳለፈውና አዲሱን የውድድር ዓመት ከሀዋሳ ከተማ ጋር የጀመረው የብሔራዊ ቡድኑ የረጅም ጊዜ ቀዳሚ ተመራጭ የሆነው ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ነው። ከ2019 ጀምሮ ሀገሩን ማገልገል የጀመረው ይህ ግብ ጠባቂ በ 23 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል።
ሌላኛው ጥሪ የተደረገለት ተጫዋች ሲሞን ፒተር ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት በዐማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረገ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መድን መፈረም የቻለው ይህ ተጫዋች በዚህ የውድድር ዓመት ወደ አዲስ አዳጊው ንግድ ባንክ መቀላቀሉ ይታወሳል። በ2009 የሀገሩን ብሔራዊ ቡድን ማገልገል የጀመረው ይህ ተጫዋች በሦስት ጨዋታዎችም ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን ከዓመታት በኋላም ሀገሩን እንዲያገለግል ጥሪ ደርሶታል።