የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ለብሔራዊ ቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዋና አሰልጣኙ ውበቱ አባተ ጋር ከተለያየ በኋላ በቴክኒካል ዳይሬክተሩ ዳንኤል ገብረማርያም እየተመራ ሁለት ጨዋታዎች ማካሄዱ ይታወሳል። ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣዩ ወር ለሚጀምረው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ በአዲስ አሰልጣኝ እንሲቀርብ ፌደሬሽኑ አማራጮችን በማየት ላይ መሆኑም ታውቋል።
ስለ አሰልጣኝ ቅጥር በተነሳ ቁጥር ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ተደጋጋሚ ጊዜ ስማቸው የሚነሳው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አሁንም ስማቸው ከቡድኑ ጋር እየተያያዘ ይገኛል። ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ግለሰቦች እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የበላይ አመራሮች ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እና ከኢትዮጵያ መድን እግርኳስ ክለብ አንዳንድ አመራሮች መደበኛ ያልሆነ (Informal) ውይይቶች አካሂደዋል። ይህንን ዜና እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ መድን ባለፈው የውድድር ዓመት ውጤታማ ጊዜ ያሳለፈውን አሰልጣኝ የመልቀቅ ፍላጎት እንደሌለውም ለማወቅ ችለናል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ቀዳሚ ተመራጭ ያደረገውን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ለመሾም ጥረቱን ይቀጥላል ተብሎ ሲጠበቅ ፌደሬሽኑ ከኢትዮጵያ መድን ጋር የሚያደርገው ውይይትም የሂደቱን ሁኔታ ይወስነዋል።