ፋሲል ከነማን ከኢትዮጵያ መድን ያገናኘው የምሽቱ መርሐግብር ብርቱ ፉክክር ተደርጎበት 1-1 ተጠናቋል።
የምሽቱ መርሐግብር ፋሲል ከነማን ከኢትዮጵያ መድን ሲያገናኝ ሁለቱም ቡድኖች ከባለፈው ጨዋታቸው አንፃር በተመሳሳይ የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርገዋል። ዐፄዎቹ ዮናታን ፍሰሐን አሳርፈው ኢዮብ ማቲያስን ፣ መድኖች አቡበከር ወንድሙን አሳርፈው ብሩክ ሙሉጌታን ተክተዋል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመሩት ፋሲሎች 5ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሱራፌል ዳኛቸው ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያደረገውን ድንቅ ሙከራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በግሩም ብቃት አስወጥቶታል።
ጨዋታው በክፍት እንቅስቃሴዎች ታጅቦ በኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ለመውሰድ ፉክክር እየተደረገበት ሲቀጥል መድኖች የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን 16ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። ሀቢብ ከማል በቀኝ መስመር ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ሳማኬ ሚኬል በቀላሉ ይዞታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ በነበሩት 10 ደቂቃዎች በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ብልጫውን የወሰዱት መድኖች 21ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። የፋሲሉ የመሃል ተከላካይ ምኞት ደበበ በጫና ውስጥ ለነበረው ኢዮብ ማቲያስ ለማቀበል ሲሞክር ኳሱን ቀምቶ በቀኙ የሳጥኑ ክፍል ይዞት የገባው ሃቢብ ከማል ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ብሩክ ሙሉጌታ በቀላሉ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ዳኝነት ላይ በሚነሱ ቅሬታዎች እና በተጫዋቾች መካከል በሚደረጉ ጉሽሚያዎች ታጅቦ በቀጠለው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች 32ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ የግብ ዕድል አግኝተው ነበር። ሆኖም ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው ወገኔ ገዛኸኝ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቶበት የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
እንደ መጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁሉ በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥረት ያደረጉት ዐፄዎቹ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥ አግኝተው ነበር። ጌታነህ ከበደ ከግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ያለፈ ኳስ በሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ቢያገኝም የግቡ ስፋት በጠበበት ቦታ ላይ በደካማ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ወደኋላ ተመልሶ በቀላሉ ይዞበታል።
ከዕረፍት መልስ ፋሲሎች ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን በጋቶች ፓኖም ቃልኪዳን ዘላለምን በአማኑኤል ገብረሚካኤል ቀይረው በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ላይ ነፍስ ዘርተውበታል። በተለይም 52ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከቀኝ መስመር ያሻገረው እና ጌታነህ ከበደ በግንባሩ ገጭቶት የግቡ የግራ ቋሚ የመለሰበት ሙከራ በዐፄዎቹ በኩል አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ዕረፍት ላይ ያደረጓቸው ቅያሪዎች ውጤታማነታቸውን እያስመሰከሩ በሄዱባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች 63ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም ወገኔ ገዛኸኝ በስህተት ባቀበለው ኳስ ከሳጥን አጠገብ ሙከራ አድርጎ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ሲመልስበት በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ግን ራሱ ቃልኪዳን ዘላለም በሳጥኑ የግራ ክፍል በግሩም ሁኔታ ገፍቶ የወሰደውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻግር ኳሱን ያገኘው ሱራፌል ዳኛቸው አስቆጥሮት ፋሲል ከነማን አቻ ማድረግ ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ተቀዛቅዘው ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት ያሳለፉት መድኖች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ አንጻራዊ መነቃቃት ሲያሳዩ ዐፄዎቹም በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በፍጥነት ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ብርቱ ፉክክር እየተደረገ በሄደበት ጨዋታ በፋሲል ከነማ በኩል ሱራፌል ዳኛቸው 85ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት አክርሮ መትቶት በቀኙ የግቡ አግዳሚ የወጣበት በኢትዮጵያ መድን በኩል 86ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አቡበከር ወንድሙ ከቀኝ መስመር ለማሻማት በሚመስል መልኩ ወደ ግቡ አሻግሮት ሳማኬ ሚኬል ያስወጣበት ሙከራ ተጠቃሽ ነበሩ። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል።