“ዋጋ እያስከፈለን ያለው የአጨራረስ ችግራችን ነው” አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ
“በሁለተኛው አጋማሽ በተቻለ መጠን ኳስ ይዘን ለመጫወት ሞክረናል ፤ በዛም ውጤታማ ሆነናል” አሰልጣኝ ይታገሡ እንዳለ
ምሽት ላይ አዳማ ከተማ በኤልያስ ለገሰ ብቸኛ ግብ ወላይታ ድቻን 1ለ0 ከረታበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞቹ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ወላይታ ድቻ
ስለ ጨዋታው…
“የጨዋታው እንቅስቃሴ ጥሩ ፉክክር የነበረበት ነበር። ዕድል ከእኛ ጋር ስላልነበረ ባለቀ ሰዓት በተቆጠረብን ጎል ተሸንፈን ወጥተናል። እንቅስቃሴያችን እጅግ ጥሩ ነው። ዋጋ እያስከፈለን ያለው የአጨራረስ ችግራችን ነው። አብዛኛዎቹ ወጣቶች በመሆናቸው በሜዳ ላይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጥሩ ነው”
የግብ ዕድሎችን ስላልተጠቀሙበት ምክንያት…
“ከጉጉት የመጣ ነው። ተጫዋቾቹ በጣም ከመጓጓታቸው የተነሳ ጎል አስቆጥረው ደስታቸውን ለመግለፅ እየቸኮሉ ነው። ይህንንም ተነጋግረን ሠርተንበት የመጣነው ነገር ቢሆንም ዛሬም ማረም አልቻልንም። ትንሽም ብስለት ይጎልባቸዋል ልጅነትም ስላለባቸው። በሂደት እያረምነው እንመጣለን ብዬ አስባለሁ”
ከጨዋታው መጠናቅቅ በኋላ ስለነበረው ውዝግብ…
“ተቀያሪ ተጫዋች ተነስቶ ከሜዳ ከወጣ በኋላ እንደገና ተመልሶ ሜዳ ላይ በመግባቱ በዚህ ጉዳይ ነው ስንናገር የነበርነው። ‘ከወጣ ወይ አስወጡት ወይ ጨዋታው አስቀጥሉት’ በዚህ ምክንያት ጨዋታው የመቋረጥ ሁኔታ መፈጠሩ ቡድናችን ላይ ተፅዕኖ ተፈጥሯል። ከዚህ ውጭ የተለየ ነገር የለም”
አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ
ስለ ጨዋታው…
“ብዙ ጊዜ የማታ ጨዋታዎች ፍጥነት የበዛባቸው እና አስቸጋሪ ጨዋታዎች ናቸው። ኳሶቻችን ቶሎ ቶሎ ይቆራረጡብን ነበር። ያው ግን እንደ ሁለተኛ ጨዋታ መጥፎ አይደለም”
ተጋጣሚያቸውን እንደጠበቁት ስለማግኘታቸው…
“ድቻ ዘንድሮ ጠንካራ ቡድን ነው። አጥቂዎቻቸው በጣም ፈጣኖች ናቸው። እንደዛም ቢሆን ግን ብዙ ጊዜ ኳሶችን የምንቀማ የነበረው ከእግራችን ላይ ነው ፤ በራሳችን ኳስ ነው ሲያጠቁን የነበረው”
ከዕረፍት መልስ ተሻሽለው ስለቀረቡበት ምክንያት…
“ለመሻሻላችን ምክንያቱ ቅያሪ ነው። በሁለተኛው አጋማሽ በተቻለ መጠን ኳስ ይዘን ለመጫወት ሞክረናል ፤ በዛም ውጤታማ ሆነናል”