ሃዋሳ ከተማ በኢዮብ ዓለማየሁ ድንቅ ግብ ሻሸመኔ ከተማን 1-0 መርታት ችሏል።
በሳምንቱ የመጨረሻ መርሐ-ግብር ሻሸመኔ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ተገናኝተዋል። ሻሸመኔዎች በወላይታ ድቻ ሽንፈት ከገጠመው አሰላለፍ ውስጥ በሦስቱ ላይ ለውጦችን አድርገዋል። ኢዮብ ገብረማርያም ፣ አሸናፊ ጥሩነህ እና ሙሉቀን ታሪኩን አሳርፈው በምትካቸው ምንተስኖት ከበደ ፣ አብዱልከሪም ቃሲም እና ዩጋንዳዊውን አጥቂ አለን ካይዋ ተክተው ሲቀርቡ ከፋሲል ጋር አቻ በተለያዩት ሀዋሳዎች በኩል በተደረጉ ሁለት ለውጦች ፅዮን መርዕድን በቻርለስ ሉክዋጎ ፣ አብዱልባሲጥ ከማልን በዳዊት ታደሰ ተክተው ቀርበዋል።
ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጥሩ አጀማመር ያደረጉት ሀዋሳዎች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገው ነበር። ሆኖም የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ውስጥ ውጤታማ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዋል።
ቀስ በቀስ በጨዋታው ላይ ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ የተጋጣሚን የግብ ክልል መፈተሽ የቻሉት ሻሸመኔዎች በተለይም ከመስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሙከራ አድርገዋል። በሁለቱም በኩል በሚቆራረጡ ቅብብሎች የታጀበው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይም የሻሸመኔ ከተማው ቻላቸው መንበሩ ሚሊዮን ሰለሞን ከሳጥን አጠገብ በሠራበት ጥፋት ጉዳት አስተናግዶ በያሬድ ዳዊት ተቀይሮ ወጥቷል። በአጋማሹም ሁለቱም ቡድኖች አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ሳያደርጉ ወደ መልበሻ ዕረፍት አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ሁሉ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ያደረጉት ሻሸመኔዎች 48ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት የሚችሉበት አጋጣሚ አግኝተው ነበር። አብዱልከሪም ቃሲም ከሳጥን ጠርዝ ላይ ያገኘውን ንጹህ የግብ ዕድል በግራው ቋሚ በኩል በወጣ ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።
ከነበሩበት የቀዝቃዘ የመጫወት ፍላጎት ወጥተው ወደ ከፍተኛ የጨዋታ ግለት የተመለሱት ኃይቆቹ 55ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። ሰለሞን ወዴሳ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ሙጅብ ቃሲም በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ መልሶበታል።
በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ከወሰዱ በኋላ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት ሃዋሳዎች 62ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ኢዮብ ዓለማየሁ ከሳጥን አጠገብ ወደ ግራው የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ በአስደናቂ ሁኔታ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ በጨዋታ ሳምንቱ ከሳጥን ውጪ የተቆጠረ አራተኛ ግብ ሆኗል። በአንድ ደቂቃ ልዩነትም ግብ አስቆጣሪው ኢዮብ ዓለማየሁ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን አሻግሮ የፈጠረው የግብን ዕድል ተከላካዩ ምንተስኖት ከበደ በግንባር ገጭቶ በማስወጣት አቋርጦታል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒው ተቀዛቅዘው የቀረቡት ሻሸመኔዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ሳይረጋጉ በሚወጡበት የጨዋታ ሂደት 73ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ሊቆጠርባቸው ነበር። በኃይቆቹ በኩል ተቀይሮ የገባው ተባረክ ፋሞ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ሆኖም በተመሳሳይ ሂደት በቀጠለው ጨዋታ 87ኛው ደቂቃ ላይ በሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ጥሩ የግብ ዕድል አግኝተው ተቀይሮ የገባው ፉዓድ መሐመድ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በጭማሪ ደቂቃዎች ውስጥም የሀዋሳው ሙጅብ ቃሲም ከሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት በመምታት ሙከራ አድርጎ በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል። ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።