የባህርዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የቡድኑ የመስመር አጥቂ ዱሬሳ ሹቢሳን ሰሞነኛ የውዝግብ ጉዳይን በተመለከተ ለሶከር ኢትዮጵያ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
የእግርኳስን ዕድገቱን በአዳማ ከተማ ወጣት ቡድን ካደረገ በኋላ በመቀጠል በከፍተኛ ሊጉ አርሲ ነገሌ አስከትሎም ወደ ሰበታ ከተማ ተጉዞ ተጫውቷል። በ2014 ነሐሴ ወር ላይ ባህርዳር ከተማን በሁለት ዓመት ውል በመቀላቀል በክለቡ ግልጋሎት እየሰጠ አሳልፏል ፣ የመስመር አጥቂው ዱሬሳ ሹቢሳ ከክለቡ ጋር የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ጨዋታዎችን እንዲሁም ከቀናቶች በፊት ባህርዳር ከተማ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን ከመድን ጋር አከናውኖ ሽንፈት ሲያስተናግድም ተጫዋቹ ተሰልፎ ለቡድኑ ግልጋሎት ሰጥቷል። ከቡድኑ ጋር በያዝነው ዓመት እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ የውል ኮንትራት ያለው ዱሬሳ ከሰሞኑ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱ ይታወሳል።
ይህንን ጉዳይም ተከትሎ የክለቡ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ስለ ተፈጠው ጉዳይ የፕሪምየር ሊጉ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታቸው መጠናቀቅ በኋላ በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
“ይሄንን ጉዳይ ባለቤቱ ምላሽ ይስጥበት ነው የምለው እንደ ቡድን ግን ባህርዳር ከተማ ጥሩ መሆኑ ፣ ጥሩ መንቀሳቀሱ የማያስደስታቸው እንደሚኖሩ እናውቃለን። ሆኖም በቡድኑ ውስጥ ገብተው ቡድኑን የሚበጥብጡ አሉ ፣ የቡድኑን ሰላም አንድነት የማናጋት ሥራዎች እየተሠሩ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። እኛ በተቻለን መጠን ተጫዋቾቻችንን አንድ አድርገን ለማልያቸው ታምነው የተሻለ ነገርን እንዲሰሩ ጥረት ማድረግ ነው ከእኛ የሚጠበቀው ፤ በተረፈ እንግዲህ ዱሬሳ ለእኛ ጠቃሚ ተጫዋቻችን ነው ፤ በ2015 የውድድር ዓመት ትልቅ ግልጋሎት የሰጠን ተጫዋች ነው። ለሀገርም የሚጠቅም ተጫዋች ነው ፣ ዱሬሳ እንግዲህ ብቃቱን ለማምጣት ጥረት እያደረግን ነው። እንደታየው ባለፉት አራት የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች በሜዳ ላይ ግልጋሎት የሰጠበት ሁኔታ ነው ያለው እንደውም የመጨረሻ የቱኒዚያ ወሳኝ ጨዋታ የመጀመሪያ ተሰላፊ ሆኖ ሜዳ ላይ የገባበት ሁኔታ ነበር አሁንም ወደዚህ ከመጣን በኋላ የመጀመሪያውን የመድን ጨዋታ በፕሪምየር ሊጉ ስናደርግ ተሰልፎ የተጫወተበት ሁኔታ ነው ያለው ፣ ነገር ግን ያው በዓምና ብቃቱ ላይ ስላልሆነ ያለው ወደነበረበት አቅሙ ለማምጣት ጥረት እያደረግን ባለንበት ሁኔታ እንግዲህ ለእኛም እንግዳ በሆነ ነገር ከቡድኑ ፍቃድ ጠይቆ ወጥቶ አልተመለሰም። በወሬ ደረጃ እኛ እንደ ማንኛውም እንደምንሰማው ከሀገር ወጥቷል ይላሉ እዚህ አለ ይላሉ ፤ እውነታውን የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው። እንደ አጠቃላይ ቡድናችን ላይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ጥረት እያደረግን ነው የተጫዋቾቹ መንፈስም ጥሩ ነው።”