በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር መቻል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-1 ተለያይተዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር መቻል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲገናኙ መቻሎች በባህር ዳር ከተረታው ስብስባቸው በአራቱ ላይ ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ግርማ ዲሳሳ ፣ በኃይሉ ግርማ ፣ ከነዓን ማርክነህ እና ምንይሉ ወንድሙ አርፈው ምንተስኖት አዳነ ፣ ግሩም ሀጎስ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ቺጂኦኪ ናምዲ ሲተኩ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው የሀዲያው ድላቸው ላይ የተጠቀሙበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ቀርበዋል።
9 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በየታየባቸው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች መቻሎች በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም በፈቱዲን ጀማል የሚመራውን የንግድ ባንክን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ሳጥን ውስጥ ለመግባት ተቸግረዋል። ሆኖም ግን 15ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የመጀመሪያ ሙከራ ሲያደርጉ በረከት ደስታ ከሽመልስ በቀለ በተቀበለው ኳስ ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።
የኋላ መስመራቸውን በማረጋጋት ቀስ በቀስ የተሳኩ ቅብብሎችን በማድረግ ወደፊት እየሄዱ ለማጥቃት የሚሞክሩት ባንኮች 28ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ባሲሩ ዑማር ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ከማቀበል አማራጭ ጋር ያገኘው ኪቲካ ጅማ በጥሩ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
መቻሎች መሃል ሜዳው ላይ በተወሰደባቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ከነበራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲቀዛቀዙ ባንኮች ባንጻሩ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ይበልጥ ተጋግለው ቀጥለዋል። በዚህ ግለታቸውም 38ኛው ደቂቃ ላይ በፉዓድ ፈረጃ ጥሩ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። በአጋማሹ የመጨረሻ ጥቂት ደቂቃዎችም መቻሎች በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር መታተራቸውን ቢቀጥሉም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ ቀዝቃዛ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ባይታይባቸውም ቀስ በቀስ ጨዋታው እየተሻሻለ ሄዷል። በዚህም ከመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናክረው የተመለሱት መቻሎች 64ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ሽመልስ በቀለ በጥሩ ዕይታ ያሾለከለትን ኳስ ያገኘው ናይጄሪያዊው ቺጂኦኬ ናምዲ አኩኔት ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን አግዶበት ወርቃማውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በአንድ ደቂቃ ልዩነትም በረከት ደስታ ከሳጥን አጠገብ ሽመልስ በቀለ ደግሞ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረጓቸውን ሙከራዎችም ግብ ጠባቂው መልሷቸዋል።
ጨዋታው በየጥቂት ደቂቃዎች ግለቱ እየጨመረ እና እየቀነሰ በሁለቱም በኩል ጥቂት የማጥቃት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉበት ሲቀጥል ንግድ ባንኮች 70ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ሊያስቆጥሩ ተቃርበው ነበር። በቀኝ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት ሱሌማን ሀሚድ ሲያሻማ ኳሱን ያገኘው ኪቲካ ጅማ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል። ያንኑ ኳስ በፈጣን የመልሶ የማጥቃት እንቅስቃሴ የወሰዱት መቻሎችም ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው የመሃል ተከላካዩ ተስፋዬ ታምራት ተደርቦ አቋርጦባቸዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ በተለይም በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው በተደጋጋሚ የግብ ሳጥን መድረስ ሲችሉ 82ኛው ደቂቃ ላይ የፈጠሩትን ንጹህ የግብ ዕድልም የመቻሉ ግሩም ሀጎስ አምክኖባቸዋል። ተጫዋቹም ኳሱን አቋርጦ በሚያስወጣበት አጋጣሚ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ ወጥቷል።
ጨዋታው በንግድ ባንክ አሸናፊነት ሊጠናቀቅ የተቃረበ ቢመስልም ግን በተጨመሩ 6 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ በመቻል በኩል ተቀይሮ የገባው ምንይሉ ወንድሙ ራሱ ላይ በተሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሮት ጨዋታው 1-1 ሊጠናቀቅ ችሏል።