ኢትዮጵያ ቡና 0-2 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በሚልኪያስ አበራ
ቅዳሜ ጥቅምት 15 ቀን 2007 ዓ.ም.
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲጀመር በመጀመሪያው የአዲስ አበባ ስታዲየም የጨዋታ መርሃ ግብር የተገናኙት ከአራት ቀናት በፊት በዚሁ ስታዲየም የአዲስ አበባ ከተማ ካስትል ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚዋች የነበሩት ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ናቸው፡፡
የመጀመርያ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና(4-4-2)
– ጌቱ ተስፋዬ
-ዴቪድበሻህ (በአስቻለው ግርማ ተቀይሮ ወጥቷል) ፣ ሚልዮን በየነ ፣ ኤፍሬም የወንድወሰን ፣ ሮቤል ግርማ
-ጥላሁን ወልዴ ፣ ደረጄ ሃይሉ ፣ መስኡድ መሃመድ ፣ ሚካኤል በየነ (በሳሙኤል ወንድሙ ተቀይሮ ወጥቷል)
-አቢኮዬ ሻኪሩ ፣ ቢንያም አሰፋ (በኤደም ካዶዞ ተቀይሮ ወጥቷል)
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (3-5-2)
– ቢንያም አሰፋ
-ቢንያም ሲራጅ ፣ አቤል አበበ ፣ አለምነህ ግርማ
– አዲሱ ካሳ ፣ ኤፍሬም አሻሞ(በዋለልኝ ገብሬ ተቀይሮ ወጥቷል) ፣ ታዲዮስ ወልዴ ፣ ስንታለም ተሻገር ፣ ሲሳይ ቶሊ
– አብዱልከሪም ሃሰን ፣ ፊሊፕ ዳውዚ (በአኪም አካንዴ ተቀይሮ ወጥቷል)
ፎርሜሽን
በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ-ጊዜ ቡድኖቹ ይዘውት የገቡት ፎርሜሽን ወይም የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አሰላለፍ ይህንን ይመስል ነበር፡፡ (ምስል 1)
ንግድ ባንኮች ከዚህ በፊትም የሚታወቁበትን የ3-5-2 በጨዋታ ሒደት ወደ 3-5-1-1 ሊቀየር በሚችል መልኩ የተጠቀሙ ሲሆን ቡናዎች ደግሞ ጠባቡን የ4-4-2 ዳይመንድ (በአብዛኛው 4-1-3-2 ነበር፤ ምክንያቱም ደረጄ ኃይሉ በጣም ወደ ኃላ እየተሳበ ( ወደ ተከላካዮች ተጠግቶ ስለተጫወተ) ተግባራዊ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡
የባንክ Back-3
ንግድ ባንኮች በሶስት የመሃል ተከላካዮች እና በሁለት የክንፍ ተከላካዮች (Wing-Backs) በመታገዝ የተደራጀ የመከላከል ቅርፅ በመያዝ የነበራቸው ብቃት ጥሩ ነበር፡፡ ሁለቱ የባንክ የመስመር (የክንፍ ተከላካዮች) ተጫዋቾች በተለምዶ ከሚታወቀው ሚዛናዊ የሆነ የማጥቃትም የመከላከልም ስራ በመከላከሉ ላይ በማተኮራቸው የቡድናቸውን የመከላከል አቅም በጥሩ ሁኔታ ሲያሳድጉ ታይተዋል፡፡ ይህም የባንክ የተከላካይ መስመር ወደ 5 በማስቀየር ቡድኑ 5-3-1-1 (5-3-2) የሚጫወት አስመስሎታል፡፡
ብዙውን ጊዜ እንደሚታወቀው አንድ ቡድን 3-5-2 ተግባራዊ ለማድረግ ሲፈለግ በሚከተሉት ሁኔታዋች ላይ ተመስርቶ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡
1) ቡድኑ በማጥቃት እንቅስቃሴ የሜዳውን ወርድ በሁለት Wing-Backs ለመጠቀም ሲፈልግ፡፡
ይህ አጨዋወት 3-5-2 የሚጠቀመው ቡድን ከመሃከለኛው የሜዳው ክፍል ምንም አይነት የተጨዋቾች ቁጥር ሳይቀንስ የማጥቃት አማራጭን አጨዋወትን በሜዳው የጎንዮሽ ክፍል ለመጠቀም ያስችላል
2) በሁለት የመሃል አጥቂዎች የሚጫወቱ የተጋጣሚ ቡድኖችን ለመከላከል የሚደረግ ምርጫ ነው፡፡
ይህም በመሃል ተከላካይ ስፍራ ላይ ተጨማሪ ከለላ ወይም ጥበቃ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህኛው ሲስተም (አጨዋወት) ሁለቱ የመሃል ተከላካዮች ሁለቱን የተጋጣሚ አጥቂዎች ማርክ የማድረግ ተግባራችውን አንደኛው ደግሞ ለነሱ ሽፋን (Cover) ወይም ከለላ (Guard) ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኳስ በራስ ቡድን ቀጥጥር ስር ሲሆን ደግሞ ከቦታው በመነሳት የሊቤሮነትን ሚና በመወጣት የመሃል ክፍል የቁጥር ብልጫ በማስገኘት የማጥቃት አጨዋወትን ሊያግዝ ይችላል፡፡
3) ይሄኛው ደግሞ ጣልያኖች አብዛኛውን ጊዜ ብቁ የመስመር አማካዮች ወይም የመስመር ተከላካዮች እጥረት ሲያጋጥማቸው እንደ መፍትሄ የሚወስዱት መንገድ ነው፡፡
- የመሃል ተጫዋቾችን ቁጥር ከፍ በማድረግ የመሃል ሜዳ የበላይነትን ለመቆጣጠር የሚል ይሆናል፡፡
ከእነዚህ 3 የተለያዩ ጥቅሞች በመነሳት የንግድ ባንክ ቡድን በጨዋታው የወሰደው የBack-3 ምርጫ የመጀመሪውን ምክንያት ያማከለ ይመስላል፡፡ ከተጋጣሚው ቡድን አንፃር (ቡና በ2 አጥቂዎች በመጫወቱ) ለተከላካይመስመሩሽፋንወይምከለላመስጠትንያለመይመስላል፡፡በጨዋታውለዚህማስረጃሊሆኑየሚበ28ኛው ደቂቃ ላይ የቡናው አጥቂ ቢንያም አሰፋ በንግድ ባንክ የጐል ክልል ጥሩ ኳስ ይዞ የባንክ ተከላካዮች (በተለይ ሁለቱ የመሃል ተከላካዮች) ኳሱን ለማስጣል ያደረጉት ጥረት እና አንደኛው ተከላካይ (አቤል) ከኃላ ሆኖ በንቃት እንቅስቃሴውን የተቆጣጠረበት መንገድ ለዚህ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ተከላካዮቹ አጥቂው (ቢንያም) ኳስ የማቀበያ አማራጮችን (Passing lanes) ያሳጡበት መንገድ የንግድ ባንክን በጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ላይ እንደሚገኝ ሊያሳይ ይችላል፡፡
የቡና የመስመር ተከላካዮች ድክመት
ብዙውን ጊዜ 3-5-2/3-5-1-1 ለተጋጣሚ ቡድኖች (በተለይ በ4-4-2/4-2-3-1/4-3-3) የሚሰጠው ጥቅም የታወቀ ነው፡፡ የፎርሜሽኑም የአተገባበር አብይ ህፀፅ የሚመነጨው ከክንፍ ተከላካዮቹ ኃላ እና ፊት የሚኖረው ሰፊ ክፍተት ነው፡፡ የባንክ የክንፍ ተከላካዮች በአብዛኛው ሲከላከሉ በታየበት ጨዋታ ላይ ከፊት ለፊታቸው የከፈቱትን ትልቅ የመጫወቻ ቦታ የቡና የመስመር ተከላካዮች (ሮቤል እና ዴቪድ) ሲጠቀሙበት አልተስተዋለም፡፡ ባንኮች የመሃል ሜዳውን Compact (ጥቅጥቅ በማለት) በመሆን በያዙት ወቅት የቡና የመስመር አማካዮችን ለመርዳት የመስመር ተከላካዮች (Full Backs) የተወጡት ሚና አናሳ ነበር፡፡ በዕለቱ የታየው ታክቲካዊ ስህተት ይሄ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ከሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ዴቪድ በሻህ በተሻለ የነበረውን ክፍት የመጫወቻ ቦታ (Space) ከፊት ለፊቱ ካለው ጥላሁን ወልዴ ጋር በመግባባት ለመሸፈን ቢሞክርም አመርቂ የሆነ ለውጥ ማሳየት አልቻለም፡፡ በግራ በኩል የነበረው ሮቤል ደግሞ ከፊት ለፊቱ የነበረው ሚካኤል በየነ ለመርዳት ያደረገው አስተዋፅኦ እጅግ አናሳ እንደነበር መመልከት ይችላል፡፡ ለሁለቱም ጐሎች መቆጠር ምክንያት የሆነው ስህተት የተፈፀመውም ከእነዚህ ቦታዎች መሆኑ በቦታው ላይ ችግር እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡
በጨዋታው ቡና በተደጋጋሚ አስጊ ያልሆኑ የጐል ሙከራዎችን ቢያደርግም አብዛኞቹ ኳሶች የሚሾልኩት በተጠቀጠቀው የባንክ ክፍል እንጂ ከመስመር ተከላካዮቹ በተደረገ እገዛ እንዳልነበረ ታይቷል፡፡ ተከላካዮቹ (ሮቤልና ዴቪድ) በላይኛው የሜዳው ክፍል ለመገኘት የማጥቃት መስመር አማራጮችን መፍጠርና (Overlap) እንዲሁም በመስመር ላይ የሚኖርን የቁጥር ብልጫ ማስገኘት ሲኖርባቸው እነሱ ግን በአብዛኛው በራሳቸው የመከላከያ ወረዳ ቆመው ነው ያመሹት (በተለይ ሮቤል)፡፡ (ምስል 2)
የአብዱልከሪም የታክቲክ ግንዛቤ
የንግድ ባንኩ ተደራቢ አጥቂ (በጨዋታው) በሜዳው ከተመለከትኳቸው ተጫዋቸች በሙሉ በታክቲክ ግንዛቤው የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለው፡፡ ቡድኑ (ባንክ) ጨዋታውን ሲጀምር በ3-5-2 ቢሆንም አብዱልከሪም ግን ከአጣማሪ አጥቂው የጐንዮሽ ጥምረት በመገንጠል በቁመት በመጣመር በፊልፕ ዳውዚ እና በአማካይ ክፍሉ መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ ሲያገለግል ነበር፡፡ ቡድኑም የጨዋታ ቅርፅን በተደጋጋሚ እንዲቀይር በማድረግ ያደረገው አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም፡፡ ኳስ በተጋጣሚ ቁጥጥር ስር ስትሆን የመሃል ሜዳው ላይ በመገኝት ቡድኑ የተደራጀ የመከላከል ቅርፅ እንዲይዝ (3-6-1 የሚመስል) ሲያደርግ ውሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቡናውን አማካይ ደረጄ ኃይሉን እንቅስቃሴ በመገደብና ይበልጥ ለራሱ ተከላካዮች ተጠግቶ እንዲጫወት በማድረግ የመጫወቻ ቦታ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ተጠቃሽ ነበር፡፡ ይህ ጥረቱ ደግሞ በመስዑድ እና በደረጄ መካከል ያለውን ርቀት አስፍቶታል፡፡ መስዑድም ተመልሶ ቡና 4-1-3-2 የሚመስል አጨዋወት የተገበረ የመሰለንም ለዚህ ነው፡፡
ለሁለተኛው የፊሊፕ ዳውዚ ጐል መገኘት ያደረገው አስተዋፅኦም ቀላል አልነበረም፡፡ በተለይ በመስመሮች መካከል ሆኖ ኳስን የተቀበለበት መንገድ ተደናቂ ነበር፡፡
Bravo አብዱልከሪም (ምስል 3)
የተጨዋቾችቅያሬ
ዴቪድ በ አስቻለው
በሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የተደረጉ ቅያሬዎችን ስናይ የቡናው አሰልጣኝ ጥላሁን ከእረፍት በኃላ ዴቪድ በሻህን አስወጥተው አስቻለው ግርማን አስገቡ፡፡ ቅያሬው ታክቲካዊ ነበር፡፡ አስቻለው ሲገባ ጥላሁን የቦታ ለውጥ በማድረግ የመስመር ተከላካነት ሚናውን መወጣት ጀመረ፡፡ ይህ ደግሞ በመጠኑም ቢሆን የቡናን የማጥቃት እንቅስቃሴ ያሳደገ ነበር፡፡ ለዚህም በተደጋጋሚ ለተደረጉት የቡና የጐል ማግባት ሙከራዎች አስተዋፅኦ ያደረገ ነበር፡፡ ጥላሁን ከፊቱ የነበረውን ሰፊ ክፍተት ያለ ፍርሃት በጥንቃቄ የሚጠቀም ደፋር ተጫዋች ነው፡፡
ሳሙኤል በ ሚካኤል
ሚካኤል በየነ ወጥቶ ሳሙኤል ወንድሙ ሲገባ የተፈጠረ ለውጥ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ከለውጡ በኋላም በሮቤል እና አስቻለው መካከል ሰፊ ክፍትተ ነበር፡፡ ይህ ክፍተት ለሁለተኛው ጐል መቆጠር አንዱ ምክንያት ነበር፡፡
-በመጨረሻ አካባቢ ለተገኘችው የፍፁም ቅጣት ምት እድል አስቻለው ከኳስ ውጪ ያደረገው እንቅስቃሴ የባንኩን አቤል ለስህተት የዳረገች ነበረች ፡፡ ምንምእንኳንጐልባይቆጠርም፡፡
የባንክ ቅያሬዎች
የባንኩ አሰልጣኝ ፀጋዬ ብዙም ከታክቲካዊ ጉዳዮች ጋር ያልተያያዘ እንደነበረ አመላካችነው፡፡ ከዕረፍት በፊት በ32ኛው ደቂቃ አካባቢ ኤፍሬም አሻሞ (በጉዳት ይመስላል) ወጥቶ ዋለልኝ ገብሬ እንዲሁም በ86ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ፊሊፕ ዳውዚን አስወጥተው ያስገቡት ሌላኛውን ናይጄሪያዊ አጥቂ አኪም አካንዴን ነበር፡፡