የሦስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በትናንትናው ዕለት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች መቋጫውን አግኝቷል። እስካሁን ድረስ በተካሄዱት ጨዋታዎች ሊነሱ ይገባቸዋል ያልናቸውን ትኩረት የሳቡ ዐበይት ጉዳዮች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።
የተሻሻለው አቤል ያለው!
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ስለ ተጫዋቾች የጎላ አስተዋፅዖ ከተነሳ የአቤል ያለውን ስም አለማንሳት ንፉግነት ነው። በሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦች አስቆጥሮ በቡድኑ ውጤት የጎላ ድርሻ ያለው ይህ ተጫዋች በርካታ ኮከቦቹን ያጣውን የፈረሠኞቹ ስብስብ ለመምራት ኮርቻው ላይ ተቆናጧል።
ባለፉት የውድድር ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ወጥነት የተሳነው ብቃት ያስመለከተን ይህ ተጫዋች አሁን ከሳምንት ሳምንት የፈረሠኞቹ ደጋፊዎች በጉጉት የሚጠብቁት ኮከብ ሆኗል። አቤል እስካሁን በተካሄዱት ሦስት ጨዋታዎች ካስቆጠራቸው አራት ግቦች እና በውጤቱ ከነበረው ድርሻ በተጨማሪ ግቦቹ የገቡበት መንገድም የተጫዋቹን የብቃት ጣርያ ማሳያ ናቸው።
ያ በጉዳቶች የታመሰ ፤ በሌሎች ጥላ ስር የደበዘዘ ማንነት አሁን ጊዜ ወጥቶለት የፈረሱን ልጓም አጥብቆ ይዟል ፤ የተጫዋቹ ጥሩ ወቅታዊ ብቃት እና የማያቋርጥ የግብ ማግባት ረሃብ እስከ መቼ ይዘልቃል? ጊዜ የሚመልሰው ጥያቄ ይሆናል።
ከግብ ጋር ታርቀው ከነጥብ ጋር የተኳረፉት ሻሸመኔ ከተማዎች
ከአስራ አምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ዋናው ሊግ ያደገው ሻሸመኔ ከተማ በሊጉ እስካሁን ድረስ ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻለ ብቸኛ ክለብ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በመጀመርያዎቹ ሁለት ሳምንታት ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኗቸው ቆይቷል። ይህ መጥፎ ክብረ ወሰንም ግብ ያላስቆጠረ ብቸኛው የሊጉ ክለብ አድርጓቸው ቆይቷል። ፈረሠኞቹን በገጠሙበት የሦስተኛው ሳምንት ጨዋታ ላይ ግን ምንም እንኳን ሽንፈት አስተናግደው ነጥብ ማስመዝገብ ቢሳናቸውም ሁለት ግቦች አስቆጥረው መጥፎውን ሪከርድ መቋጫ አስገኝተውለታል። በጨዋታው ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ያስቆጠረው ያሬድ ዳዊት ደግሞ ከአስራ አምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ በሻሸመኔ ማልያ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች ሆኗል። ሆኖም ቡድኑ እስካሁን ድረስ ነጥብ ማስመዝገብ አልቻለም ፤ ይህም ብቸኛው የሊጉ ክለብ ያደርገዋል። ይህንን መጥፎ ክብረወሰን ለመግታትም ሲዳማ ቡናን የሚገጥምበትን የአራተኛ ሣምንት ጨዋታ ይጠብቃል።
ታሪክ ራሱን ሲደግም!
በኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ የአንድ ለባዶ ሽንፈት አስተናግደው ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነጥብ በመጋራት ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች አንዱን ብቻ ያሳኩት ሲዳማ ቡናዎች የባለፈው ዓመት መጥፎ አጀማመራቸውን ዘንድሮም ደግመውታል። ባለፈው የውድድር ዓመትም በተመሳሳይ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዲያ ሆሳዕና ሽንፈት አስተናግዶ ከድሬዳዋ ከተማ አቻ በመለያየት ከሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ አስመዝግቦ ከባድ የውድድር ዓመት ያሳለፈው ይህ ክለብ ዘንድሮም ከወዲሁ መንገዳገድ ጀምሯል። ሆኖም ከባለፈው የውድድር ዓመት አንፃር ሲታይ ዘንድሮ አንድ በጎ ጎን አለው። ክለቡ ባለፈው የውድድር ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ያስተናገደው የግብ መጠን 11 ነበር ፤ ዘንድሮ ግን ምንም እንኳ ያስመዘገበው ነጥብ በተመሳሳይ 1 ቢሆንም የተቆጠረበት የግብ መጠን ግን 3 ብቻ ነው።
የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ውጤታማነት ከፍ ብሏል
በዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንድ እንግዳ ነገር አለ ፤ የቅጣት ምት ግቦች መብዛት። ከዚህ ቀደም በሊጋችን ደረት የሚያስነፋ የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም አልነበረም። ሦስተኛው ሳምንት ላይ በደረሰው የውድድር ዓመት ግን ከወዲሁ የጥራት ደረጃቸው ከፍ ያሉ በርካታ የቅጣት ምት ግቦች እየተመለከትን እንገኛለን። እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎችም ሰባት የቅጣት ምት ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን ደጋፊውም በየሳምንቱ ሁለት እና ከሁለት በላይ ቆንጆ የቅጣት ምት ግቦች ተመልክቷል። በርካታ ተጫዋቾችም በሂደቱ በግልፅ የሚታይ መሻሻሎች አምጥተዋል። ከነዚህ ውስጥ ስማቸው የሚነሳ ተጫዋቾች ደግሞ በየፊናቸው ሁለት ሁለት ቅጣት ምት ያገቡት የፈረሠኞቹ አጥቂ አቤል ያለውና የዐፄዎቹ አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው ናቸው። ፍሬው ሰለሞን ፣ ተመስገን በጅሮንድ እና ያሬድ ዳዊት ደግሞ ሌሎች ከቅጣት ምት ግብ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ሆነዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከመጥፎ አጀማመር አዙሪት ተላቋል
አዲሱን ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪችን ቀጥረው ጥሩ አጀማመር ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት ጥሩ የሚባል አጀማመር አልነበራቸውም። ዘንድሮ ግን በሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሰባቱን እጃቸው ላይ አስገብተው ተከታታይ የመጥፎ አጀማመር ታሪካቸውን ሽረውታል። ክለቡ ባለፈው የውድድር ዓመት ከሦስት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ፤ ካቻምና በተመሳሳይ ወቅት ደግሞ ሁለት ነጥቦችን ብቻ ነበር የሰበሰበው። ዘንድሮ ግን ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት ተመሳሳይ ወቅት በአማካይ ሦስት ነጥቦችን ብቻ ያስመዘገበው ቡና ሁለት ብቻ ከስሮ ነጥቡን ወደ ሰባት ከፍ አድርጓል።