አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ ከሻሸመኔ ከተማ ጋር እንደማይቀጥሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከ15 ዓመታት በኋላ የመሳተፍ ዕድልን ያገኘው ሻሸመኔ ከተማ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድም ነጥብ ማስመዝገብ ሳይችል ቀርቷል። በመሆኑም ከክለቡ ውጤት ማጣት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ በፍቃዳቸው ከክለቡ ጋር ስለመለያየታቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ከክለቡ ጋር አብረው እንደማይቀጥሉ ለአመራሮች መግለፃቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ የተናገሩ ሲሆን አሁን ላይ ከቡድኑ ጋር እንደማይገኙም አረጋግጠናል። ይህንን አስመልክቶ የክለቡን ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ባይሳካም አሳልጣኙ በቡድኑ የልምምድ መርሐግብር ላይ አለመገኘታቸው የሁለቱ አካላት መጨረሻ መቃረቡን የሚጠቁም ሆኗል።
የቀድሞው የአቃቂ ቃሊቲ እና ኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ፀጋዬ ከከፍተኛ ሊጉ ካሳደጉት ክለብ ጋር በፕሪምየር ሊጉ እንደማይቀጥሉ ያሳወቁን እንጂ ክለቡ በይፋ መልቀቂያቸውን ስለመቀበሉ ያለው ነገር የሌለ ሲሆን በቀጣይ ቀናት አሰልጣኙ ይፋዊ መልቀቂያ አስገብተው ሁለቱ አካላት በስምምነት ሊለያዩ የሚችሉቡት ዕድል ለእርግጥነት የቀረበ ሆኗል።