የ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዳሜ ሲጀመር አምና የመጀመርያዎቹን ደረጃዎች ይዘው ያጠናቀቁ ክለቦች ነጥብ ጥለዋል፡፡
ቅዳሜ በተካሄደው ብቸኛ ጨዋታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያ ቡናን 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወጥቷል፡፡ በክረምቱ ከፍተኛውን የዝውውር ወጪ ያወጣው የፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ቡድን በ2 ሳምንት ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ ኢትዮጵያ ቡናን የገጠመ ሲሆን ሁለቱን በድል ተወጥቷል፡፡
የጨዋታው የመጀመርያ ግብ የተቆጠረችው የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ሰአት በዴቪድ በሻህ እና ግብ ጠባቂው ጌቱ ተስፋዬ መካከል በተፈጠረው አለመናበብ ምክንያት ነው፡፡ በሁለተኛው ግማሽ ፊሊፕ ዳውዚ በድንቅ ሁኔታ የመጣቸውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቶታል፡፡ ናይጄርያዊው ግቧን ካስቆጠረ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በመሄድ ‹‹ኢቦላ›› በሚል ሲያበሽቁት ለነበሩት ተመልካቾች ምላሽ ሰጥቷል፡፡ (ኋላ ላይ ፊሊፕ በፌስቡክ ገፁ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን ይቅርታ ጠይቋል፡፡ )
ትላንት (እሁድ) ቀሪዎቹ 6 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋዎች ተካሂደዋል፡፡ በ9፡00 አዲስ መጪው ወልድያን ያስተናገደው ደደቢት በቀላሉ 6-1 አሸንፎ አጀማመሩን አሳምሯል፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ወልድያዎች ሲሆን የቀድሞው የንግድ ባንክ አጥቂ አብይ በየነ ጨዋታው በተጀመረ በ10ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ነገር ግን የወልድያዎች መሪነት የቆየው በ14ኛው ደቂቃ ታደለ መንገሻ በግንባሩ ገጭቶ እስካስቆጠረበት ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ የወልድያው አብይ በየነ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ የተወገደ ሲሆን ደደቢትም ሙሉ ለሙሉ ጨዋታውን ተቆጣጥሮታል፡፡ የደደቢት ቀሪዎቹን ግቦች ያስቆጠሩት ሳሚ ሳኑሚ (2) ፣ ዳዊት ፍቃዱ ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ሽመክት ጉግሳ ናቸው፡፡
በሌሎች የክልል ጨዋታዎች ወደ አዳማ የተጓዘው የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮ ወደ ሊጉ ካደገው አዳማ ከነማ ጋር ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ሙገር ሲሚንቶን 1-0 ሲረታ ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ዳሽን ቢራን አስተናግዶ 1-0 ተሸንፏል፡፡ ሃዋሳ ላይ ሀዋሳ ከነማ ከአርባምንጭ ከነማ 1-1 ፤ አዲስ አበባ ላይ መብራት ኃይል ከመከላከያ 0-0 አቻ ተለያይተዋል፡፡
የሊጉን አንደኛ ሳምንት ደደቢት እና ሳሚ ሳኑሚ ከላይ ሆነው ሲጨርሱ ወልድያ ከነማ ከ5 የግብ እዳ ጋር የመጨረሻውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ሊጉ በቀጣይ አርብ እና ቅዳሜ በሚካሁዱ የ2ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡