“ከእኛ ቡድን ጋር ማንም ቡድን ቢጫወት ተመሳሳይ ሁለት መቶ ፐርሰንት ኢነርጂ ነው የሚሰጥህ” አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ
“ሜዳው ደረቅ ቢሆን እንደዚህ ዓይነት ጨዋታ ይሆናል ብዬ አላስብም ፤ የተሻለ ነገር ይኖረን ነበር” አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ
አዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 2-2 በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን ከፈፀሙ በኋላ ሁለቱም አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን አድርገዋል።
አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ
ስለ ጨዋታው …
“ቆንጆ ጨዋታ ነበር ፣ ፈጣን ጨዋታ ነበር ፣ ቅዝቃዜም ስለሆነ የተጫዋቾቹ ተነሳሽነት ጥሩ ነው።”
አየሩ ዝናባማ በመሆኑ በቡድኑ ላይ ስለፈጠረው ተፅዕኖ …
“አዎ በጉዳት ከጭቃው ጋር ተያይዞ ሁለት ተጫዋቾች ወጥተዋል ፤ ዮሴፍም አብዲሳም። ሜዳው ደረቅ ቢሆን እንደዚህ ዓይነት ጨዋታ ይሆናል ብዬ አላስብም ፤ የተሻለ ነገር ይኖረን ነበር።”
ረጅም ደቂቃ እየመሩ በመጨረሻ ደቂቃ አቻ መሆን ስለቻሉበት መዘናጋቶች…
“አንደኛው የሁለቱ ባለመግባባት ነው። ሁለተኛውም አንዳንዴ በኮንሰንትሬሽን መጨረሻ ላይ ባለው ነገር ነው ሁለቱም ኳሶች የገቡት ይሄ ደግሞ ይፈጠራል።”
በመጨረሻ ደቂቃ በዳኝነቱ ላይ ስለነበራቸው ቅሬታ…
“ለእኔ ኃይለየሱስ ትልቅ ዳኛ ነው በዚህ ጉዳይ ምንም ድርድር ውስጥ የሚገባ አይደለም። አንዳንዴ የውሳኔዎች ስህተት ለእርሱ ትክክል ይሆናል ፤ ለእኔ ትክክል አልሆነም ብዬ በማስበው ነገር ላይ ተቃውሞ አሰምቻለሁ። ይሄ ትክክል ነው እያልኩኝ አይደለም። ይቅርታ ነው ማለት የምፈልገው።”
አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከ2ለ0 ወደ 2ለ2 ስላጠናቀቁት ጨዋታ …
“ጥሩ ነው ፤ በሰው ሜዳ ላይ ነው የተጫወትነው ሜዳቸው ነው። በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር በሁለታችንም በኩል። ሁለት ለዜሮ መርተው ሁለት ዕኩል ወጥተን ለሁለታችንም ጥሩ ነው ፤ የተመጣጠነ ጨዋታ ነው ብዬ የማስበው።”
በተከታታይ ጨዋታዎች በቅያሪዎች መነሻነት ውጤት የመቀየራቸው ሥነ ልቦና…
“ትክክል ነው ፣ በሥነ ልቦና የገባውም ያልገባውም የማሸነፍ ሜንታሊቲው ትልቅ ነው። ስለዚህ ማንም ገባ ማንም የቡድኑ ቅርፅ የቡድኑ የማሸነፍ ባህል ተሸክሞ ስለሚመጣ ማድረግ ያለባቸውን ነገር ተነግሯቸው ስለሚገቡ በጣም ጥሩ ነገር እያደረጉ ነው በጣም ደስተኛ ነኝ።”
ባደረጓቸው ጨዋታዎች ሁሉ በመጀመሪያው አጋማሽ ስለሚቀዛቀዙበት ሂደት..
“ሁለት ጨዋታዎች ላይ ገብቶብን ነው የተነሳነው ጎሎች እንዴት እንደገቡ አይተሀቸዋል። ሌላው ሁለት ለባዶ ተመራን የማሸነፍ ሜንታሊቲያችን የማሸነፍ ባህላችን ትልቅ ስለሆነ በተጫዋቾቼ ኮርቼባቸዋለሁ። ከዚህም በላይ ማድረግ ይችላሉ ዝናቡ በኋላ ላይ ረብሾናል ፤ የመጫወት ዘይቤያችንን። ከዚህም በኋላም ማድረግ የሚችሉ ተጫዋቾች አሉ ጥሩ ነገር ነው ብዬ ነው የማስበው ለእኔ።”
ስለ ተጋጣሚያቸው አዳማ …
“ከእኛ ቡድን ጋር ማንም ቡድን ቢጫወት ተመሳሳይ ሁለት መቶ ፐርሰንት ኢነርጂ ነው የሚሰጥህ። ግን ተጫዋቾቼ ያላቸውን ነገር ለማድረግ ኮንሰንትሬት አድርገው ሁሌ የተሻለ ነገር ለማድረግ ስለሚሄዱ ኮርቼባቸዋለሁ በጣም ትልቅ ነገር ነው ያየውት።”