“ስለጨዋታው ይሄ ነው የምለው የለም ፣ የኳስ ፍሰት የለውም ነበር” አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ
“ማሸነፍ የሚገባንን ዕድል አሳልፈን ሰጥተናል” አሰልጣኝ አስራት አባተ
አዳማ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 2ለ1 በመርታት ካጠናቀቀው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞቹ ጋር ቆይታን አድርጋለች።
አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ
ስለጨዋታው….
“ስለ ጨዋታው ይሄ ነው የምለው የለም ፣ የኳስ ፍሰት የለውም ነበር። ትንሽ ከበድ ይል ነበር ፣ ብናገባም የበፊቱ ፖሰስ የምናደርገው ነገር የለም።”
ከመጀመሪያው አጋማሽ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ስለ መቀዛቀዛቸው…
“ብዙ ጊዜ የእንደዚህ ሰዓት ጨዋታ ሲሆን በመሉ ጉልበታቸው ላታገኛቸው ትችላለህ ተጫዋቾቹን ፣ መቀዛቀዝ ነበረ ያም ሆኖ ግን ውጤቱ ስለሚያስፈልገን ሦስት ነጥብ ልናገኝ ችለናል።”
ከጨዋታው በፊት ልምምድ አቁመዋል ስለሚባለው ጉዳይ…
“በማቆም ደረጃ ሁለት ቀን ዕረፍት ነው ያደረግነው ፣ አንዳንዴ የምታርፍባቸው ተከታታይ ተጫውተን ዕሮብ ነው ከዛ የተጫወትነው እና የነበረን ሰዓት ቅርብ ጊዜ ስለነበር ለእነዛ ማረፍ ስላለብን ነው። ከክፍያም ጋር ተያይዞ አንዳንድ ነገሮች አሉ ፣ ሂደት ነው የሚፈልገው እንደዛም ሆኖ ማኔጅመንቱ ከእኛ በላይ ያሉ ሰዎች ይሄንን ነገር የተወሰነ ጊዜ ዕረፍት ውድድሩ ሊቋረጥ ነው። ይሄንን ነገር ጨራርሰውልን ይጠብቁናል ብዬ አስባለሁ ግን አሁንም ከመስራት ወደ ኋላ አላሉም እና ከላይ ጀምሮ ያለው ተነሳሽነታቸው ጥሩ ነው ፣ ይሄንን ነገር ደግሞ ያስቀጥሉታል ብዬ አምናለሁ።”
በመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ከጥቂት ደጋፊዎች ስለተሰማው መልዕክት…
“አንዳንዴ ደጋፊ ከአንተ ጋር ነው የሚጨነቀው ግን ማልያም ለብሶ ላይደግፍክ ይችላል። ከ70 ደቂቃ በኋላ እያሉ ሰምቻቸዋለሁ አንዳንዴ ጆሮህን ከሰጠህ ኮንፊውዝ ትሆናለህ ያ ማለት ለእኔ የማይገርመኝ ከሰባ ደቂቃም በኋላ አግብቼ አሸንፌያለሁ ፣ 80 ደቂቃም ሁለት ጎል ገብቶብኝ ተሸንፌ አውቃለሁ። ይሄ ሂደት ነው በአጋጣሚዎች የሚመጡ ናቸው እና ተጫዋቾቹ የሚከፍሉትን መስዋዕትነት ስለማውቅ ብዙ አልገረመኝም። ይሄ ማለት ሁሉም ደጋፊ ነው ማለትም አይደለም ፣ አንድ ልጅ ሁለት ልጅ ሊናገር ይችላል እንጂ የአዳማ ደጋፊ በጣም ብዙ መስዋዕትነት የከፈለ አሁንም እየከፈለ ያለ ነው። እንደዚህ አይነት ነገሮች ይከሰታሉ እና ሊገርም አይገባም።”
ስላለፉት አምስት ጨዋታዎች እና ስለ ቀጣዩ የአንድ ወር ዕረፍት …
“ብዙ የሚስተካከሉ ነገሮች አሉ። ኳስ ከልምምድ ብቻ አይደለም ፣ ከልምምድ ውጪ ያሉ ነገሮች የሚስተካከሉ ይኖራሉ እና በሙሉ አቅማችን ልምምዳችንን አልሰራንም ነበር ፣ ብዙ የሚስተካከሉ አሉ ፣ ከዕረፍቱ ስንመለስ የተሻለ ቡድን እና እንቅስቃሴን ይዘን እንመጣለን።”
አሰልጣኝ አስራት አባተ – ድሬዳዋ ከተማ
ስለ ሁለቱም የጨዋታ አጋማሾች…
“ጥሩ ጨዋታ ነው ያደረግንበት ፣ እየተሸነፉ ጥሩ ማለት ይከብዳል ፣ እንግዲህ እንዳየህው በርካታ ዕድሎችን ነው የፈጠርነው ፣ ጎሎች ላይ አፈፃፀም ላይ ዛሬም ከሌላው ጊዜ በተለየ ብዙ ዕድሎችን መጨረስ አልቻልንም ግን ማሸነፍ የሚገባንን ዕድል አሳልፈን ሰጥተናል።”
በሁለቱም አርባ አምስት የጎል ዕድሎችን ፈጥረው ያለ መጠቀማቸው ምክንያት…
“የመጀመሪያው ተረጋግቶ ጎል ላይ አለመጨረስ ነው። ያለቁ ኳሶች ናቸው አራት አምስት ለቁጥር ይታክታል እስኪያልቅ ድረስ ያለው ፣ የመረጋጋት ችግር ነው። ሁለተኛ ደግሞ ጨዋታውን ለማሸነፍ ከነበረው ጉጉት እና በዛ ነው እኔ የምለው ከዚህ በፊትም በነበሩ ጨዋታዎች ላይ የጎል ዕድሎችን እናመክናለን ፣ የዛሬ ደግሞ የተለየ አድርጎታል። አስተካክሎ ስነ ልቦናቸው ላይ ሰርቶ መምጣት ነው።”
ተከታታይ ሽንፈቶቹ ቡድኑ ላይ ስለሚፈጥረው ተፅዕኖ …
“በዘንድሮው ባለው ውድድር የትኛው ቡድን ይሸነፋል ለማለት እጅግ በጣም ከባድ ነው። ቅድም እንዳልኩት እየተሸነፍክ ጥሩ ነኝ ማለት ባይቻልም ቡድኖቹ ደግሞ ሁሉም ተፎካካሪ ስለሆኑ መሸነፉ ጥሩ ባይሆንም ፣ ወደ ማሸነፉ እንመጣለን የሚል እምነት አለኝ።”
ስለ ቀጣዩ አንድ ወር በሚኖረው ዕረፍት በቡድኑ ለመስራት ስላሰቡት ነገር…
“ቡድናችን ከዕለት ወደ ዕለት እየተሻሻለ ያለ ቡድን ነው። በአጨዋወትም የጎል ዕድሎችንም በመፍጠርም እንደዚሁ እየተዋሀደ ያለ ቡድን ነው ፣ ምናልባት በተቋረጠበት ሂደት ላይ እንግዲህ ቅድም በነገርኩህ በስነ ልቦናው ላይ ፣ ጎል አፈፃፀም ላይ በይበልጥ ሰርተን ውጤታማ የሚያደርገንን አጨዋወት ይዘን መጥተን ፣ አዳብረን አንድ ነገር እንፈፅማለን።”