በምሽቱ ጨዋታ መቻል በያሬድ ከበደ ብቸኛ ግብ ሀምበሪቾን 1-0 ረቷል።
በምሽቱ መርሐግብር መቻል እና ሀምበሪቾ ተገናኝተው መቻል ድቻን ሲያሸንፍ የነበረውን ቋሚ አሰላለፍ ሳይቀይር ዛሬም ወደ ሜዳ ሲገባ ከሀድያ ጋር ያለ ጎል አጠናቀው በነበሩት ሀምበሪቾዎች በኩል ግን የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ተደርጓል።አቤል ዘውዱ እና ማናዬ ፋንቱ በብሩክ ቃልቦሬ እና ዳግም በቀለ ተተክተው ጀምረዋል።
እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው እና ለተመልካች ሳቢ የሆነ እንቅስቃሴ ባልተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ መጠነኛ ፉክክር ቢደረግበትም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ግን ሁለቱም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተቸግረዋል። የአጋማሹ ብቸኛ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራም ወደ ዕረፍት ለማምራት በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ በመቻሎች አማካኝነት ሲደረግ ሽመልስ በቀለ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ናይጄሪያዊው ቺጂኦኬ ናምዲ አኩኔቶ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ በቀላሉ ይዞበታል።
ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በሁለቱም በኩል ከቀረቡት የፍጹም ቅጣት ምት ይገባናል ጥያቄዎች እና ዳኝነት ላይ ከሚነሱ ቅሬታዎች ውጪ ትኩረት የሚስብ እንቅስቃሴ አልተደረገም። ሆኖም ግን 58ኛው ደቂቃ ላይ በሳጥኑ የግራ ክፍል ኳስ ይዞ የገባው የሀምበሪቾው አቤል ከበደ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር።
የጨዋታው የመጨረሻ 30 ደቂቃዎች በአንጻራዊነት የተሻለ ፉክክር ሲደረግባቸው በመቻል በኩል 65ኛው ደቂቃ ላይ ቺጂኦኬ ናምዲ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ በቀላሉ ሲይዝበት በአምስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ በሀምበሪቾ በኩል ተቀይሮ የገባው ዳግም በቀለ በጥሩ ሁኔታ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት በገባው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፍያን መልሶበታል።
የአጥቂ መስመራቸው ላይ ቅያሪ በማድረግ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ላይ መሻሻል ያሳዩት መቻሎች ቅያሪያቸው ፍሬ አፍርቶ 89ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ተቀይሮ የገባው ያሬድ ከበደ መቻሎች የፈጠሩት የግብ ዕድል በተከላካዮች ሲመለስ ያገኘውን ኳስ በተረጋጋ እና ብስለት በተሞላበት አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
በየጨዋታዎቹ ላይ እንደሚኖራቸው ጠንካራ እንቅስቃሴ ከውጤት ጋር መታረቅ ያልቻሉት ሀምበሪቾዎች ዛሬም ተመሳሳይ አጋጣሚ አግኝቷቸዋል። ሆኖም ግን 92ኛው ደቂቃ ላይ አልአዛር አድማሱ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ዳግም በቀለ በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ጨዋታውም በመቻል 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።