ሦስት ክለቦችን በጋራ አቅፎ የተመሠረተው የሸገር ከተማ 26 የሚጠጉ ተጫዋቾችን አስፈርሞ ወደ ውድድር ይገባል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ በአዲስ ስያሜ ብቅ ያለው ሸገር ከተማ በምድብ ለ ላይ ተደልድሎ ውድድሩን ከነገ ጀምሮ ማከናወን ይጀምራል። ለገጣፎ ለገዳዲ ፣ ገላን ከተማ እና ሱሉልታ ከተማን በአንድ ላይ በማቀፍ ሸገር ከተማ በሚል የተመሠረተው ክለቡ ለገጣፎ ለገዳዲን ከከፍተኛ ሊጉ ጀምሮ እስከ ፕሪምየር ሊጉ ያሰለጠኑትን አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ እና ተጨማሪ ረዳት አሰልጣኞችን በአዲስ መልኩ ካወቀረ በኋላ ሀያ ስድስት የሚደርሱ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ መቀላቀሉን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ይፋ አድርጓል።
ከተቀላቀሉት ሦስት ክለቦች የተካተቱ ተጫዋቾችን ስንመለከት ዓምና በፕሪምየር ሊጉ በነበረው ለገጣፎ ለገዳዲ የሚታወሱት ተከላካዮቹ ታምራት አየለ ፣ መዝገቡ ቶላ ፣ አስናቀ ተስፋዬ ፣ አማካዩ ተፈራ አንለይ እና ግብ ጠባቂው ሚኪያስ ጆጂ ይገኛሉ። በከፍተኛ ሊጉ ጠንካራ ተፋላሚ በነበረው ገላን ከተማ የተጫወቱት ተከላካዮቹ ሲሳይ ጥበቡ እና አረጋኸኝ ማሩ እንዲሁም አማካዮቹ ምንተስኖት መንግሥቱ እና ክንድአለም ፍቃዱ በአዲሱ ሸገር ከተማ ተካተዋል። በሱሉልታ ከተማ ከነበሩ ተጫዋቾች ደግሞ ግብ ጠባቂው አብረሀም ኃይሌ እና አማካዩ ፍቃዱ እልሁ ዘንድሮ ለሸገር ይጫወታሉ።
በክለቡ ስብስብ ውስጥ የተካተቱ በፕሪምየር ሊጉ የሚታወሱ ተጫዋቾችን ስንመለከት ለስድስት የሊጉ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው ዱላ ሙላቱን ጨምሮ በኢትዮጵያ ቡና ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና በወላይታ ድቻ የተጫወተው ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ ፣ በለገጣፎ ፣ ፋሲል ከነማ እና አምና በባህር ዳር ከተማ ያሳለፈው አጥቂው ፋሲል አስማማው ፣ በኢትዮጵያ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ስልጤ ወራቤ የተጫወተው አጥቂው ሳዲቅ ሴቾ ፣ በኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመስመር አጥቂ የነበረው አላዛር ሽመልስ ፣ በደቡብ ፖሊስ ፣ ሀዋሳ እና ኢትዮጵያ ቡና የተጫወተው ተከላካዩ ዘነበ ከድር ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካዩ ሚራጅ ሰፋ እና በአዲስ አበባ ከተማ እና ስልጣ ወራቤ የሚታወሰው አማካዩ ሙኸጅር መኪ ለሸገር ከተማ ፈርመዋል።
በተጨማሪም ለቡራዩ ከተማ የተጫወቱት ተከላካዩ ጌታቸው ገብረመስቀል እና አጥቂው አብዲ ሁሴን ፣ ለሮቤ ከተማ የተጫወተው ተከላካዩ ታሪኩ እሸቴ ፣ በአምቦ አማካይ የነበረው ነብዩ ንጉሴ ፣ የንግድ ባንክ የመስመር አጥቂ የነበረው ሀይከን ድዋሙ ፣ ከመድን ከ20 ዓመት በታች የተገኘው አጥቂ መሐመድ ኑረዲን እና የደብረብርሀን አማካይ የነበረው ካሳሁን ሰቦቃ የሸገር ከተማ ተጫዋቾች ሆነዋል።
ሸገር ከተማ ነገ 10:00 ላይ አርባምንጭ ከተማን በመግጠም በታሪኩ የመጀመሪያውን የሊግ ጨዋታ ያከናውናል።