የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬ በተከናወኑ 8 ጨዋታዎች ሲጠናቀቅ የምድብ ለ ጨዋታዎች በሙሉ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
ምድብ ሀ
የእለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡናን ከነቀምቴ ከተማ አገናኝቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ይርጋጨፌ ቡና ጥሩ እና የተሻለ እንቅስቃሴ አስመልክቶናል። በጨዋታውም ግብ ለማስቆጠር ተጭኖ ሲጫወት ተስተውሏል። በአንፃሩ ነቀምቴ ከተማ የቀዘቀዘ እንቅስቃሴ እና መከላከልን ምርጫ በማድረግ ምላሽ ሰጥቷል። በ30ኛው ደቂቃ ይርጋ ጨፌ ቡና በይድነቃቸው ውበቱ ጥሩ አጨራረስ ግብ አስቆጥሮ አጋማሹን እየመራ አገባዷል።
ከእረፍት መልስ ነቀምቴ ከተማ እጅጉን ተሽሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያረግ ተስተውሏል። ይህንን ተከትሎ ነቀምት ከተማ በተደጋጋጋሚ ወደ ይርጋጨፌ ቡና የግብ ክልል በመድረስ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርጓል። በ78ኛው ደቂቃ ነቀምቴ ከተማ ያገኘውን የግብ እድል ተመስገን ዱባ በአግባቡ ተጠቅሞ በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል። በግቡ የተነቃቁት ነቀምቴ ከተማዎች በገባባቸው ግብ እጅጉን የተረበሹት ይርጋጨፌ ቡና ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ባደረጉት ጥረት በ86ኛው ደቂቃ በተሰራባቸው ጥፋት ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ተመስገን ዱባ ማስቆጠር ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ሁለት የይርጋጨፌ ቡና ተጫዋች የሆኑት ምናሴ ወጋየው እና ዘላለም አበራ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል። ጨዋታውም በነቀምቴ 2-1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ነቀምቴ የምድቡን መሪ በሦስት ነጥቦች ርቀት መከተሉን ቀጥሏል።
የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ወለዲያን ከጅማ አባ ቡና አገናኝቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እና ፈጣን እንቅስቃሴ ተመልክተናል። በግብ በታጀበው አጋማሽ ወልድያ ኳስን መሠረት በማድረግ በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ ሲጥር ተስተውሏል። ጅማ አባ ቡናን በአጭር ቅብብሎች ላይ በመመስረት የግብ ዕድል ለመፍጠር ሞክሯል። በ20ኛው ደቂቃ ጅማ አባ ቡና ያገኘውን የግብ ዕድል በአብዱል አዚዝ ዘነቡ አስቆጥሯል። ብዙም ሳይቆይ በ22ኛው ደቂቃ ወልድያ በቢንያም ላንቃሞ አማካኝነት ግብ አስቆጥሮ አፀፋውን መመለስ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ጅማ አባ ቡና ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርጓል። በ34ኛው ደቂቃ ጅማ አባ ቡና ከብሩክ ዮሐንስ የተሻገረለትን ኳስ ጴጥሮስ ገዛኸኝ ወደ ግብ ቀይሮታል። ጅማ አባ ቡና አሁንም በተደጋጋሚ ጫና ፈጥሮ ተጫውቶ በ40ኛው ደቂቃ በእስጢፋኖስ ተማም አማካኝነት ተጨማሪ ግብ አስቆጥሯል። በዚሁ ውጤት አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ወልድያ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተጫዋች ቅያሪ አድርገው ቢገቡም ውጤታማ መሆን ተስኗቸዋል። በአንፃሩ ጅማ አባ ቡና የወሰደውን የግብ ልዩነት ለማስጠበቅ የተከላካይ ስፍራቸውን አጠናክረው በሚያገኙት ኳስ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድል ሲፈጥር ተስተውሏል። ይህንንም ተከትሎ ጅማ አባ ቡና በ75ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን የግብ ዕድል በድጋሚ እስጢፋኖስ ተማም አስቆጥሮ የቡድኑን የግብ መጠን ከፍ አድርጓል። 4-1 መርታት የቻለው አባ ቡና የዓመቱን የመጀመሪያ 3 ነጥብ ማሳካት ችሏል።
የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋርን ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ አገናኝቷል። ቀዳሚው አጋማሽ ጥሩ እና ፈጣን አጨዋወት የተመለከትንበት አጋማሽ ሆኗል። ጅማ አባ ጅፋር ኳስን ተቆጣጥሮ በጥሩ ፍሰት ወደ ግብ ለመድረስ ጠረት ሲያረግ ተስተውሏል። በአንፃሩ ኦሮሚያ ፖሊስ ኃይልን የቀላቀለ አጨዋወት እና የመልሶ ማጥቃትን አጨዋወት ምርጫ በማድረግ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ተስተውሏል። ይህንንም ተከትሎ በ18ኛው ደቂቃ ኦሮሚያ ፖሊስ ከመዕዘን ምት ተሻግሮ የተጨራረፈውን ኳስ ኤፍሬም ገረመው ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ይህን የሚባል የግብ ሙከራ ሳንመለከት አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ጅማ አባ ጅፋር የተጫዋች ቅያሪ አድርገው የተሻለ አጨዋወት ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በዚህም አጨዋወት በ71ኛው ደቂቃ ላይ ገለታ ኃይሉ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ኢሳያስ ታደለ ግልፅ የግብ ዕድል ሳይጠቀም ቀርቷል። ኦሮሚያ ፖሊስ በመልሶ ማጥቃት ግልፅ የግብ እድል አግኝቶ ሳይጠቀም ቀርቷል። ጨዋታውም በኦሮሚያ ፖሊስ 1-0 አሸናፊነት ተደምድሟል።
የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ንብን ከስልጤ ወራቤ አገናኝቷል። በጨዋታው ጥሩ የሚባል ፉክክር እና የአልሸነፍም ባይነት መንፈስ ተመልክተናል። በአጋማሹ ስልጤ ወራቤ ኳስን ይዘው ወደ ፊት በመሄድ ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ተስተውሏል። ጠንካራ የተከላካይ ስፍራ ያለው ንብ ኳስን ለተጋጣሚው ለቆ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጥረት አርገዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ በዚሁ አጨዋወት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከእረፍት መልስ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ አጨዋወት እና ጥሩ ፉክክር አሳይተውናል። በ60ኛው ደቂቃ የስልጤ ወራቤ ተጫዋች የሆነው ንሳሃ ታፈሰ ከርቀት አክርሮ መትቶ ግብ አስቆጥሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላ በሁለቱም ቡድኖች ፍጥነት የበዛበት አጨዋወት አስመልክተውናል። በ86ኛው ደቂቃ የስልጤ ወራቤ ግብ ጠባቂ ፍቅሩ ወዴሳ ከግብ ክልሉ ውጪ ጥፋት በመስራቱ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ይሄን ክፍተት ለመጠቀም ንብ ተጭኖ ሲጫወት በ89ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ምስክር መለሰ የመታውን ኳስ በግብ ጠባቂው መዘናጋት ወደ ግብ ተቀይሯል። ጨዋታውም በ1-1 ውጤት ተፈፅሟል።
ምድብ ለ
ዛሬ በምድብ ለ በሀዋሳ አርተፊሻል ሜዳ አራት ጨዋታዎች ተደረገው አራቱም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆን 8 ግቦችም ተቆጠረዋል።
ጠዋት 3:00 የጀመረው አርባምንጭ ከተማን ከደሴ ከተማ ያገነኛው መረሃ ግብር አራት ግቦች ሲቆጠሩበት ደሴ ከተማ ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስቶ ነጥብ መጋራት ችሏል።
የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ከፍተኛ የሆነ የመከላከል እና የመፈራራት ሰሜት በታየበት በዚህ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ የበላይነት ብልጫ በመውሰድ የመጀመሪያ አጋማሽ ያለግብ ሊጠናቀቅ ተጨማሪ ደቂቃ ተጨምሮ ሽርፍራፍ ደቂቃዎች ቀርተውት እያለ የአርባምንጩ የፊት መስመር ተከላካይ በእርስ በርስ ቅብብሎሽ ያገኘውን አጋጣሚ ወደግብነት ቀይሮ ዕረፍት 1-0 እየመሩ መውጣት ችለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የአቻነት ግብ አብዝተው ሲፈልጉ እና ኳስን ተቆጠጣረው ሲጫወቱ የተስተዋሉት ደሴ ከተማዎች አምበላቸው ሚካኤል ለማ ከመስመር የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በተመረጠው በአቡሽ ደርቤ አማካኝነት የተሻገረለትን ኳስ ወደግብ በመቀየር አቻ ማድረግ ችሏል።
አርባምንጭ ከተማዎች መሪ ለመሆን በመልሶ ማጥቃት የደሴን ግብ ክልል በሚደርሱበት ሰዓት በ68ኛው ደቂቃ ላይ በአሸናፊ በቀለ ላይ ጥፋት ተሰርቶበት ፍፁም ቅጣት ምት ያገኙ ሲሆን በላይ ገዛኸኝ አስቆጥሮ ዳግሚ መሪ እንዲሆኑ አስችሏቸው የነበረ ቢሆንም በመሪነት የቆዩት ለሁለት ያህል ደቂቃ ብቻ ነበር። ተቀይሮ የገባው አብዱልአዚዝ ዳውድ ያገኙትን ቅጣት ምት በ70ኛው ደቂቃ በርቀት መትቶ በማስቆጠር ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ አድርጓል።
በማስከተል ቢሾፍቱ ከተማን ከነጌሌ አርሲ ያገናኘው የ5:00 ሰዓቱ ጨዋታ ያለግብ የተጠናቀቀ ሲሆን ነጌሌ ከተማ መሪነቱ የሚያጠናክርበትን ዕድል ሳይጠቀም ቀርቷል።
ሁለቱም ቡድኖች እምብዛም የግብ ሙከራዎችን ባላደረጉበት በዚህ ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ መጨረሻ አከባቢ በተለይም መደበኛው አስር ደቂቃዎች ሲቀሩት ነጌሌ አርሲዎች ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አልቻለም።
ቀን 8:00 ሰዓት ላይ በተደረገው በሌላኛው ጨዋታ አዲስ ከተማ ከ ቦዲቲ ከተማ ተጋናኝተው 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። የመጀመሪያ አጋማሽ ድንቅ ብቃት ያሳዩት ቦዲቲ ከተማዎች የመጀመሪያውን አጋማሽ እየመሩ የወጡ ሲሆን ጨዋታ ከተጀመረ በ17ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረለት ኳስ መልካሙ በኬ ወደግብነት ቀይሮ ዕረፍት እየመሩ መውጣት ችለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር በማድረግ የአቻነት ግብ ለማግኘት በተደጋጋሚ ሲሞክሩ የተስተዋሉት አዲስ ከተማዎች በ61ኛው ደቂቃ እርስ በርስ ቅብብሎሽ ወደ ሳጥን ውስጥ ጥሶ በመግባት በበረከት ብርሃን አማካኝነት ግብ በማስቆጠር አቻ በመሆን ጨዋታው 1-1 በአቻ ውጤት ጨርሰዋል።
በምድቡ የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በሆነው መርሃ ግብር ጋሞ ጨንቻ ከ ወሎ ኮምቦልቻ የገናኙ ሲሆን በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሌላኛው ጨዋታ ሆኗል።
በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ግቦች የተቆጠሩ ት በፍፁም ቅጣት ምት ሲሆን የወሎ ኮምቦልቻን ግብ ማኑሄ ጌታቸው እና የጋሞ ጨንቻውን ግብ ታደሰ ፈለቀ አስቆጥረው ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል።
የወሎ ኮምቦልቻን መሪነት ግብ ማኑሄ ጌታቸው ገና በ9ኛው ተቂቃ በራሱ ላይ የተሰራበትን ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግንተው ወደግብነት ቀይሮ መሪ ማድረግ ችሎ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያ አጋማሽ እየመሩ መውጣት ችለዋል። በሁለተኛው አጋማሽ በመልሶ ማጥቃት ግብ ሲፈልጉ የታዩት ጋሞ ጨንቻዎች በእርስ በርስ ቅብብሎሽ ወደ ተቃራኒ ቡድን በመግቡበት ወቅት በእጅ ተነክቶ ፍፁም ቅጣት ተሰቷቸው ተቀይሮ የገባው ታደሰ ፈለቀ ወደ ግብነት ቀይሮ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከሦስት ቀናት ዕረፍት በኋላ ሰኞ ወደ ጨዋታ እንደሚመለስ ይጠበቃል።