እጅግ ከፍተኛ በሆነ የመጨረሻ ደቂቃ ውዝግብ ለ17 ደቂቃዎች የተቋረጠው ጨዋታ በመጨረሻም በጣና ሞገዶቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በምሽቱ መርሐግብር ባህር ዳር ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ሲገናኙ የጣና ሞገዶቹ በስድስተኛው ሣምንት ፈረሠኞቹን 2ለ1 የረታው ስብስባቸው ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ለጨዋታው ሲቀርቡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3ለ0 በተሸነፉት ኃይቆቹ በኩል ግን የ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ተደርጓል። በዚህም ሰለሞን ወዴሳ ፣ እንየው ካሳሁን ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና አማኑኤል ጎበና በ አቤኔዘር ኦቴ ፣ አቤኔዘር ዮሐንስ ፣ ማይክል ኦቱሉ እና ኢዮብ ዓለማየሁ ተተክተው ገብተዋል።
12፡00 ሲል በተጀመረው ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ በቁጥር በዝተው በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት ብልጫውን መውሰድ ሲችሉ 4ኛው ደቂቃ ላይም የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ከሳጥን ውጪ በአለልኝ አዘነ አማካኝነት ማድረግ ችለዋል። በአንጻሩ ሀዋሳዎች ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲቸገሩ ተስተውሏል።
ጨዋታው 12ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ባህርዳሮች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ፍራኦል መንግሥቱ ከረጅም ርቀት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ አስወጥቶት ያ ኳስ በግራ መስመር ከማዕዘን ሲሻማ ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ ያገኘው ቸርነት ጉግሳ የግብ ጠባቂውን እጅ ጥሳ የገባች ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ጨዋታውን መምራት ከጀመሩ በኋላም ይበልጥ እየተጋጋሉ በመሄድ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ማድረግ የቀጠሉት የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ተጫዋቾች 17ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ዓባይነት ፌኖ ከፍራኦል መንግሥቱ በተሻገረለት ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ያደረገውን ግሩም ሙከራ ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ይዞበታል።
የተጋጣሚያቸውን ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ለመቋቋም የተቸገሩት ሀዋሳዎች በጨዋታው የመጀመሪያውን ሙከራቸውን 28ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ የተሰጠውን የቅጣት ምት ሙጅብ ቃሲም ወደ ግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶበታል። በተመለሰው ኳስም ባህርዳሮች ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገው ሀብታሙ ታደሰ እና የአብሥራ ተስፋዬ የወሰዱት ኳስ በመጨረሻም ፍጹም ጥላሁን ወደ ግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ አግዶበታል።
ከነበራቸው ግለት እየተቀዛቀዙ የሄዱት የጣና ሞገዶቹ 40ኛው ደቂቃ ላይ ግን በተመሳሳይ አጨዋዎት መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ፍራኦል መንግሥቱ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ከፍጹም ጥላሁን እና ከፍሬዘር ካሳ ንክኪዎች በኋላ ያገኘው ቸርነት ጉግሣ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎት ለራሱም ሆነ ለክለቡ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል።
ጨዋታውን በሚፈለገው ሂደት ማስኬድ ያልቻሉት የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ተጫዋቾች ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ግብ 44ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል። ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ በረጅሙ ለመምታት የሞከረው ኳስ ላይ ስህተት በመሥራቱ ከሙጅብ ቃሲም እግር ጋር ሲያጋጨው የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ታፈሰ ሰለሞን እጅግ ማራኪ በሆነ ክህሎት ተከላካይ አሸማቆ በመሸወድ እና ግብ ጠባቂውን በተቃራኒ አቅጣጫ በመጣል ተረጋግቶ ግብ አድርጎታል።
ከዕረፍት መልስ እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ጥሩ የኳስ ቁጥጥር እና የማጥቃት እንቅስቃሴ የያዙት ሀዋሳዎች በተለይም 55ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት በወሰዱት ኳስ በሙጅብ ቃሲም አማካኝነት ያደረጉት ሙከራ እና ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ የመለሰበት አጋጣሚ አስቆጪ የነበር ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም በተመሳሳይ እንቅስቃሴ የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም ታፈሰ ሰለሞን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ቀስ በቀስ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ 72ኛው ደቂቃ ላይ በሀብታሙ ታደሰ አማካኝነት ካደረጉት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ውጪ በሁለቱም በኩል የጠራ የግብ ዕድል አልተፈጠረም ነበር።
ሆኖም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመጠኑ በማስመለስ ጨዋታውን ማረጋጋት የቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች ጨዋታውን ማረጋጋት ሲችሉ ሀዋሳዎችም 86ኛው ደቂቃ ላይ ሙጅብ ቃሲም ከሳጥን አጠገብ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ የአቻነት ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ 2-1 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ተቃርቦ ነበር።
እጅግ ከፍተኛ ውዝግብ በመፈጠሩ ጨዋታው ለ 17 ደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዷል። የሀዋሳው አጥቂ ሙጅብ ቃሲም ከቀኝ መስመር በተሻገረለት ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ይመልስበታል። በዚሁ ቅፅበት ዋና ዳኛው ዳንኤል ይታገሡ ግብ ነው ብለው ቢያጸድቁም ሁለተኛ ረዳት ዳኛ የነበሩት መሐመድ ሁሴን ግቡ ከመስመር እንዳላለፈ እና መጽደቅ እንደሌለበት ተናግረው ግቡ እንዲሻር አድርገዋል። ውሳኔውን ተከትሎም እጅግ ከፍተኛ ቅሬታ ያሰሙት ሀዋሳዎች ጨዋታውን ለማቋረጥ ወስነው ለ 17 ደቂቃዎች አቋርጠውት በኋላም ከውጪ በመጡ የዳኞች ኮሚቴ አባላት አግባቢነት ወደ ጨዋታው ቢመለሱም ጨዋታው በአንድ ደቂቃ ልዩነት በባህርዳር ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የጣና ሞገዶቹ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጨዋታው ጠንካራ እና አላስፈላጊ ግጭቶች የበዙበት እንደነበር ጠቁመው በቡድናችው ተጫዋቾች ላይ መሻሻሎችን እያዩ እንደሆነ በመናገር ውዝግብ ያስነሳው ግብም መሻሩ ትክክል እንደሆነ ገልጸዋል። የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው በእንቅስቃሴ ደረጃ ከመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች በኋላ የተሻሉ እንደነበሩ እና ሽንፈቱም ይበልጥ እንደሚያጠናክራቸው በመናገር ውዝግብ ያስነሳው ግብ መጽደቅ እንደነበረበት በመጠቆም የዕለቱን ዳኝነት “የወረደ ዳኝነት” ሲሉ ኮንነዋል።