የዘንድሮ የውድድር ጊዜ እንዳሰበው ያልሆነለት ሲዳማ ቡና የቀድሞ አሰልጣኙን መቅጠሩ ታውቋል።
በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እየተመራ የዘንድሮውን ውድድር ጅማሮውን ያደረገው ሲዳማ ቡና ገና በአምስተኛው ሳምንት ነበር ከውጤት መጥፋት ጋር ተያይዞ ከአሰልጣኙ ጋር በስምምነት የተለያየው። የክለቡ አመራሮችም ሌላ ዋና አሰልጣኝ እስኪያፈላልጉ ድረስ በጊዜያዊነት በምክትል አሰልጣኙ አረጋዊ ወንድሙ እንዲመራ በማድረግ ያለፉትን የሦስት ሳምንት ጨዋታዎችን ሲመሩ ቆይተዋል።
በዚህ ሒደት ውስጥ የቡድኑን አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን የተቀመጡት የክለቡ የቦርድ አመራሮች ይሆናሉ ብለው ባሰቧቸው አሰልጣኞች ዙርያ ሰፊ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በመጨረሻም የቀድሞ አሰልጣኙ ዘላለም ሽፈራውን የቡድኑ አሰልጣኝ አድርገው ለመቅጠር ተስማምቷል። በሁለቱም መካከል ይፋዊ የፊርማ ስምምነቱ የተጠናቀቀ ሲሆን ለአንድ ዓመት ውል በማሰር ከቀናት ዕረፍት በኋላ ለሊጉ ውድድር ዝግጅቱን የፊታችን ቅዳሜ ሲጀምር አሰልጣኝ ዘላለም ቡድኑን ማዘጋጀት ስራቸውን እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ዘላለም ከዚህ ቀደም ደቡብ ፖሊስ፣ በደደቢት፣ አዳማ ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ወልዲያ፣ ወላይታ ድቻ እና ሰበታ ከተማን ያሰለጡኑ ሲሆን ሲዳማ ቡናን ከ2007 ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ዓመት ማሰልጠናቸው አይዘነጋም።