በኢትዮጵያ ዋንጫ ሦስተኛ ዙር የመጀመሪያ ቀን አዳማ ላይ የሚደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድታናል።
ሁለተኛ ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ከህዳር 15 እስከ 17 መካሄዳቸው ይታወሳል። አስራ ስድስት ክለቦች የሚያሳትፈው የሦስተኛው ዙር መርሀ ግብር ደግሞ ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀምራል።
ነጌሌ አርሲ ከ ኢትዮጵያ መድን
የከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ መሪው አርሲ ነገሌ ከ ኢትዮጵያ መድን የሚያረጉት የሦስተኛ ዙር መክፈቻ ጨዋታ 07:00 ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ይከናወናል።
በከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ እየተሳተፈ የሚገኘው ነገሌ አርሲ በአስራ ሰባት ነጥቦች ምድቡን እየመራ ይገኛል። ነገሌዎች በሁለተኛው ዙር ስልጤ ወራቤን ሦስት ለባዶ አሸንፈው ነበር ወደዚህ ዙር የተሻገሩት ቅዳሜ ታህሳስ ስድስት ባካሄዱት የመጨረሻው የሊግ ጨዋታቸውም ከየካ ክፍለ ከተማ ጋር አንድ አቻ ተለያይተዋል። ነገሌ አርሲዎች ለስድስት ሳምንታት ግቡን ሳያስደፍር የቆየ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አላቸው። በሰባት ጨዋታዎች የተቆጠረባቸው የግብ መጠንም የየካ ክፍለ
ከተማው ብስራት ታምሩ ያስቆጠረባቸው አንድ ግብ ብቻ ነው። ቡድኑ በከፍተኛ ሊጉ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች በአምስቱ ድል ሲቀዳጅ በሁለት ደግሞ አቻ ተለያይቷል ፤ ዘጠኝ ግቦች አስቆጥሮም አንድ ግብ ብቻ አስተናግዷል።
ባለፈው የውድድር ዓመት በፕሪምየር ሊጉ ባሳዩት ድንቅ ብቃት የአህጉራዊ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ተቃርበው የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች ባለፈው የውድድር ዓመት ያልሰመረላቸውን በአህጉራዊ ውድድሮች የመሳተፍ ህልም ከረዥም ዓመታት በኋላ ለማሳካት በኢትዮጵያ ዋንጫ እየተሳተፉ ይገኛሉ። መድኖች በሁለተኛው ዙር በችኩሜካ ጎድሰ እና ያሬድ ዳርዛ ግቦች ታግዘው ድሬዳዋ ከተማን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ነው ወደ ሦስተኛው ዙር የተሻገሩት። በፕሪምየር ሊጉ ከተከታታይ ስድስት የአቻና የሽንፈት ውጤቶች በኋላ ሀምበሪቾን ሁለት ለአንድ አሸንፈው ከሳምንታት ቆይታ በኋላ ከድል ጋር የታረቁት መድኖች ከብዙ ጥበቃ በኋላ ያገኙትን የአሸናፊነት መንፈስ ለማስቀጠል በነገው ዕለት ከከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ መሪ ክለብ ጋር ይጫወታሉ።
ደብረ ብርሀን ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
በነገው ዕለት እዛው አዳማ ላይ የሚከናወነው ሌላኛው የውድድሩ ሦስተኛ ዙር ጨዋታ እንደመጀመሪያው ሁሉ የፕሪሚየር ሊግ ክለብን ከከፍተኛ ሊግ ክለብ ያገናኛል።
በከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ተደልድለው ጨዋታዎቻቸው በማካሄድ የሚገኙት ደብረ ብርሃኖች ከሰባት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦች ሰብስበው በአስረኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ደብረብርሀን ከተማዎች በሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ጋሞ ጨንቻን በመለያ ምት አሸንፈው ነበር ወደ ሦስተኛው ዙር የሚያሳልፋቸው ውጤት ያስመዘገቡት። በመጨረሻው የከፍተኛ ሊግ ጨዋታም በተመሳሳይ ጋሞ ጨንቻን ሁለት ለአንድ አሸንፈው ፋሲል ከነማን ይገጥማሉ። ቡድኑ ከአራተኛው ሳምንት በከፋ ቡና ከደረሰበት የአንድ ለባዶ ሽንፈት በኋላ ሽንፈት አላስተናገደም። ሁለት ድልና አንድ የአቻ ውጤት ሲያስመዘግብ በሦስት ጨዋታም ሰባት ግቦች አስቆጥሯል።
በወላይታ ድቻ እና ሀድያ ሆሳዕና ከደረሰባቸው ተከታታይ የሊግ ሽንፈት በኋላ ወደዚህ ጨዋታ የሚገቡት ዐፄዎቹ በሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ላይ በምኞት ደበበ እና ፍቃዱ ዓለሙ ግቦች ታግዘው ነቀምት ከተማን ሦስት ለባዶ በማሸነፍ ነው ወደ ሦስተኛ ዙር የተሻገሩት። በ2011 የኢትዮጵያ ዋንጫ አንስተው ክለቡ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በአህጉራዊ ውድድር እንዲሳተፍ ያስቻሉት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከዓመታት በኋላ በተመለሰው ውድድር ላይ ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ ለመሆን በሚያደርጉት ጉዞ የከፍተኛ ሊግ ተወዳዳሪው ደብረ ብርሀንን ይገጥማሉ። በጨዋታውም የክለቡ ተጫዋች አማኑኤል ገብረሚካኤል የቀድሞ ክለቡን ይገጥማል።