ዛሬ በአዳማ ሣ/ቴ/ዩ ስታዲየም በተጀመረው የኢትዮጵያ ዋንጫ ሦስተኛ ዙር ኢትዮጵያ መድን እና ፋሲል ከነማ ተጋጣሚያቸውን በመርታት ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
በሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች ድል የቀናቸውን 16 ክለቦች በመያዝ የሚደረገው የኢትዮጵያ ዋንጫ ሦሰተኛ ዙር ዛሬ በአዳማ ሣይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጅማሮውን አድርጓል።
7 ሰዓት ላይ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነጌሌ አርሲን ከኢትዮጵያ መድን አገናኝቷል። ኢትዮጵያ መድን ጨዋታውን መቆጣጠር ሲችል ነገሌ አርሲዎች በአንጻሩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል። ጨዋታው በዚሁ ቀጥሎ 31ኛው ደቂቃ ላይ በመድኖች በኩል ኦሊሴማ ቺኔዱ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ የነጌሌ አርሲው ግብ ጠባቂ አሸብር ተስፋዬ ሲመልሰው ያንኑ ኳስ ያገኘው በርናንድ ኦቼንግ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ነጌሌ አርሲዎች ግብ ለማስቆጠር የተሻለ እንቅስቀሴ ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል። ይህንን ተከትሎም ግብ ለማስቆጠር ወደ ፊት ተጭነው በሚጫወቱበት አጋጣሚ በሚተውት ቦታ ደግሞ ኢትዮጵያ መድኖች በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድል ሊፈጥሩበት ጥረት አድርገዋል። 44ኛው ደቂቃ ላይም መስፍን ዋሼ ከመሃል ሜዳ በተሻገረለት ኳስ በመግፋት ግብ ጠባቂ እና ተከላካይ አልፎ ለማስቆጠር ሲሞክር በአባቱ ዓለሙ ጥፋት ተሠርቶበት የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት ቹኩዌሜካ ጉድሰን አስቆጥሮት አጋማሹ በኢትዮጵያ መድን 2-0 መሪነት ተጠናቆ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል ነጌሌዎች የተወሰደባቸውን የግብ ብልጫ ለመቀልበስ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ወደ ሳጥን በመድረስ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አርገዋል። መድኖች በአንጻሩ በመጀመሪያ አጋማሽ ያገኙትን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋዎት በመምረጥ የሚያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል። 82ኛው ደቂቃ ላይም ነጌሌ አርሲ ያገኘውን የማዕዘን ምት ሙሉቀን ተስፋዬ እና ሰለሞን ገመቹ እዛው ካስጀመሩት በኋላ ወደ ግብ ክልል የተሻማውን ኳስ ያገኘው ታምራት ኢያሱ ማስቆጠር ሲችል ከግቧ መቆጠር በኋላም ነጌሌ አርሲ ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። 89ኛው ደቂቃ ላይ የነጌሌ አርሲ ምክትል አሰልጣኝ የሆነው ቴቤሶ ደስታ የዋና ዳኛውን ውሳኔ ባልተገባ ሁኔታ በመቃወሙ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ መድን 2-1 አሸናፊነት ተጠናቆ ኢትዮጵያ መድን ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፍ ችሏል።
9:30 ላይ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ደብረ ብርሃን ከተማን ከፋሲል ከነማ አገናኝቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የሚባል አጀማመር ማድረግ ሲችሉ ደብረ ብርሃን ከተማ በኳስ ቁጥጥሩ ከፋሲል ተሽለው ተገኝተዋል። በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች ኃይል በቀላቀለ አጨዋወት እና በረጃጅም ኳስ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። ሆኖም በአጋማሹ ያን ያህል ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተጋግሎ ሲቀጥል በሁለቱም ቡድኖች በኩል ብርቱ የሆነ ፉክክር ተደርጎበታል። ዐፄዎቹም ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሻሽለው በመቅረብ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ የደብረ ብርሃን ከተማን ግብ መፈተናቸውን ሲቀጥሉ በአንጻሩ ደብረ ብርሃኖች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። 73ኛው ደቂቃ ላይም ፋሲል ከነማዎች ግብ ለማስቆጠር ጥረት በሚያደርጉበት አጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ፍቃዱ አለሙ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል። ጨዋታውም በፋሲል ከነማ 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ዐፄዎቹ ወደ ሩብ ፍፃሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።