የኢትዮጵያ ዋንጫ ሦስተኛ ዙር ነገም ሲቀጥል አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ አራት የፕሪምየር ሊጉን ክለቦች የሚያገናኙት ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ሀድያ ሆሳዕና ከ ወላይታ ድቻ
በፕሪምየር ሊጉ በተመሳሳይ ስምንት ነጥቦች ሰብስበው በግብ ክፍያ የሚበላለጡ ሁለት ተቀራራቢ ብቃት ያላቸው ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ አምስተኛውን አላፊ ቡድን ይለያል።
በሁለተኛው ዙር በተመስገን ብርሀኑ ብቸኛ ግብ ንግድ ባንክን አሸንፈው ወደ ሦስተኛው ዙር የተሻገሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ወላይታ ድቻን ይገጥማሉ። ሀድያ ሆሳዕናዎች በፕሪምየር ሊጉ ከተከታታይ አምስት አቻዎች በኋላ ፋሲል ከነማን አሸንፈው የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሦስት ነጥብ አግኝተዋል። በነገው ዕለትም የአሸናፊነት መንገዱ አስቀጥለው ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በመጨረሻዎቹ ሦስት ግንኙነቶች ቡድኑን ካላሸነፈው ወላይታ ድቻን ይገጥማሉ። ቡድኑ የጦና ንቦችን በገጠመባቸው ሦስት የመጨረሻ ጨዋታዎች ሁለቱን ስያሸንፍ በአንዱ አቻ ተለያይቷል።
በሁለተኛው ዙር ከቢንያም ፍቅሩ፣ ፀጋዬ ብርሀኑና ዮናታን ኤልያስ በተገኙ ሦስት ግቦች ደሴ ከተማን ሦስት ለአንድ አሸንፈው ወደዚ ዙር የበቁት የጦና ንቦች በውድድሩ ለመቆየት ሀድያ ሆሳዕናን ይገጥማሉ። በፕሪምየር ሊጉ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ከሁለት ግብ በላይ ተቆጥሮባቸው ከቆየ በኋላ በሲዳማ ቡናን በገጠሙበት ጨዋታ ላይ አራት ግቦች ያስተናገዱት የጦና ንቦች ዳግም ወደ አፍሪካ መድረክ ለመቅረብ በዚ ጨዋታ ጥሩ ውጤት ማምጣት ይጠበቅባቸዋል። የጦና ንቦቹ ከሰባት ዓመታት በፊት በአሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ መሪነት በአፍሪካ መድረክ መሳተፍ ችለው ነበር፤ በወቅቱም የግብፁ ዛማሌክን በመለያ ምቶች ያሸነፉበት ጨዋታ አይረሳም።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሻሸመኔ ከተማ
ከሳምንታት በፊት አምስት ግቦችና ማራኪ እንቅስቃሴ የነበረው ጨዋታ ያስመለከቱን ሁለት ክለቦች በነገው ዕለት በኢትዮጵያ ዋንጫ በሚያደርጉት ጨዋታ ሩብ ፍፃሜውን ለመቀላቀል ይፋለማሉ።
.
የሁለተኛ ዙር መክፈቻ በነበረው ጨዋታ ሀምበሪቾን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ወደ ሦስተኛው ዙር ያለፉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በነገው ዕለት ሻሸመኔ ከተማን ይገጥማሉ። ፈረሰኞቹ በፕሪምየር ሊጉ ከውድድር ዓመቱ ብቸኛ ሽንፈት መልስ ሀዋሳ ከተማን ሦስት ለባዶ በማሸነፍ ወደ መሪዎቹ ጎራ መጠጋት ችለዋል። የግብ መጠናቸውም አስራ ስምንት በማድረስ የአጥቂ ክፍላቸው አይምሬነት አስመስክረዋል፤ በጨዋታ በአማካይ 2.7 ግቦች ያስቆጠረው የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የአጥቂ ጥምረት የሊጉ አስፈሪው የማጥቃት ጥምረት ነው። በነገው ዕለትም በጨዋታ በአማካይ 1.5 ግቦች ላስተናገደው የሻሸመኔ ተከላካይ ክፍል ትልቅ ፈተና ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሻሸመኔ ከተማዎች ካፋ ቡናን በመለያ ምት በማሸነፍ ነበር ወደ ሦስተኛው ዙር የተቀላቀሉት፤ ጎል አልባ የነበረው ጨዋታም ወደ መለያ ምት አምርቶ በሻሸመኔ አምስት ለአራት አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። ሻሸመኔዎች በውድድሩ ለመሰንበት ከሳምንታት በፊት በፕሪምየር ሊጉ ካሸነፋቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ይጫወታሉ፤ ቡድኑ በጨዋታው ሁለት ጊዜ መምራት ችሎ በመጨረሻ ሦስት ለሁለት መሸነፉም ይታወሳል።
በነገው ጨዋታም በፕሪምየር ሊጉ ማሳካት ያልቻሉትን ድል በኢትዮጵያ ዋንጫ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ለማሳካት ትልቅ ፈተና ይጠብቃቸዋል።
ቡድኑ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ከግብ አዳማ ከተማ ጋር አቻ ተለያይቶ ወደዚ ጨዋታ እንደመቅረቡ ቀላል ግምት እንዳይሰጠው ያደርጋል።