በሊጉ ተጠባቂ ከሆኑት ታሪካዊ ደርቢዎች አንዱ የሆነው የሸገር ደርቢ በነገው ዕለት ይካሄዳል ፤ ቀድሞ ከተያዘለት ቀን ተራዝሞ ነገ የሚደረገውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።
አምስት ድል አልባ ሳምንታት ያሳለፉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በስምንት ነጥቦች አስራ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በኢትዮጵያ ዋንጫ ኮልፌ ቀራንዮን ሁለት ለባዶ አሸንፎ ስራውን የጀመረው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በነገው የደርቢ ጨዋታ መጀመርያው የሊግ ጨዋታውን ይመራል፤ አሰልጣኙ በነገው ዕለት ይዞት የሚገባውን አጨዋወት ለመገመት ቢያዳግትም አብዛኛው ጊዜ ቡድኖች የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ የሚከተሉት ጥንቃቄ የታከለበት አጨዋወት ይዞ የሚገባበት ዕድል ይኖራል ተብሎ ይገመታል። ጨዋታው ደርቢ እንደመሆኑና ተጋጣሚያቸው በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ያስቆጠረ ጠንካራ የማጥቃት አጨዋወት ያለው ቡድን መሆኑም በአመዛኙ መከላከል ላይ ያተኮረ አጨዋወት ይከተላል ተብሎ ይገመታል።
በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አስር ግቦች ያስተናገደ ደካማው የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ ክፍል በነገው ዕለት ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ ይገመታል፤ የተከላካይ ክፍሉ የተጋጣሚን ጥቃት የሚመክትበት ብቃትም የጨዋታውን ውጤት ይወስነዋል። አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ የተጠቀሰው የመከላከል ችግር ላይ ስር ነቅል ለውጥ ከማድረግ ባለፈ ከተካሄዱት ሰባት ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ከአንድ ግብ በላይ ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወት ላይ ውስን ለውጥ ማድረግ ይጠበቅበታል።
አስራ ስድስት ነጥቦች ሰብስበው በአራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፈረሰኞቹ ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግና ከሽንፈት መልስ ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸው ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ፈረሰኞቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወት አላቸው፤ በተለይም በአቤል ያለው የሚመራው የፊት መስመር ጥምረቱ የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ ነው። ቡድኑ በባህርዳር ከተማ ሁለት ለአንድ ከተሸነፈበት ጨዋታ ውጭ በስድስት ጨዋታዎች ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠሩም የማጥቃት አጨዋወቱ ውጤታማነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል። በነገው ጨዋታም በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ግቦች ላስተናገደው የኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ ክፍል ከባድ ፈተና ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል። ፈረሰኞቹ በነገው ዕለት ከሌሎች ጨዋታዎች በበለጠ መስመሮች ላይ ያመዘነ የማጥቃት አጨዋወት ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል፤ ተጋጣሚያቸው ቡና የመስመር ተከላካዮች ማጥቃቱ ላይ የሚያሳትፍ ቡድን መሆኑም ቡድኑ ሁለቱም መስመሮች ዋነኛ የማጥቃት መሳርያው የሚያደርግበት ዕድል የሰፋ ነው።
በፈረሰኞቹ በኩል ቅጣት ላይ ካለው ሞሰስ አዶ በስተቀር ሙሉ ቡድኑ ለጨዋታው ዝግጁ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ያለፉትን ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ በጉዳት ምክንያት ያልተሰለፈውና በኢትዮጵያ ዋንጫ የተመለሰው አማካዩ ፍሪፖንግ ለጨዋታው ብቁ ነው። በቡናዎቹ በኩል ሬድዋን ናስር በጉዳት ወንድሜነህ ደረጄ ደግሞ በቅጣት የነገው ጨዋታ የሚያልፋቸው ይሆናል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ 46 ጊዜ ተገናኝተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ጊዮርጊስ 21 ጊዜ ድል ሲቀናው ቡና ደግሞ 7 ጊዜ አሸንፏል ፤ 18 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።
– በ46ቱ የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት በድምሩ 92 ጎሎች መረብ ላይ አርፈዋል። 62ውን ግብ በማስቆጠር ፈረሰኞቹ ቀዳሚ ሲሆኑ ቡናማዎቹ ደግሞ 30 ኳሶችን ከመረብ አዋህደዋል።