ከአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ጋር በስምምነት የተለያየው ሀምበርቾ የሹሙት ውሳኔዎችን ሲያስተላልፍ በቀጣይ በማን እንደሚመራም ታውቋል።
በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው ሀምበርቾ ካደረጋቸው ስምንት መርሀግብሮች አንድም ጨዋታ ሳያሸንፍ በ2 ነጥቦች ብቻ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል። ከዚህ ጋር በተገናኘ ከሰሞኑ አሰልጣኙ ከክለቡ ጋር እንደማይገኙ እና በቀጣይም ክለቡን ሊለቁ እንደሚችሉ ቀደም ባለው ዘገባችን ገልፀን የነበረ ሲሆን አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ከክለቡ የቦርድ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት በይፋ በዛሬው ዕለት በስምምነት መለያየታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።
የፊታችን ቅዳሜ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በ9ኛው ሳምንት ጨዋታ የሚያስተናግደው ክለቡ የቀድሞው የከንባታ ሺንሺቾ አሰልጣኝ የነበረውን አስፋው መንገሻን በቡድን መሪነት ከዚህ ቀድም ክለቡን በቡድን መሪነት ያገለገለው ጌዲዮን ተሰማን በቴክኒክ ኃላፊነት ሾሟል። በቀጣይ ቡድኑ በጊዜያዊነት በረዳት አሰልጣኞቹ መላኩ ከበደ እና ብሩክ ሲሳይ እንዲሁም በአዲሱ ቴክኒክ ኃላፊ ጌዲዮን ተሰማ የጋራ መሪነት ዋና አሰልጣኝ እስኪሾም ድረስ እንደሚመራ ታውቋል።