በአስረኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ሀዋሳ ላይ በከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ለ’ አራት ጨዋታዎች ሲደረጉ ሁለቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ኦሜድላ እና አዲስ ከተማ ክ/ከ ድል አርገዋል።
ሦስት ሰዓት ሲል በጀመረው የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ሸገር ከተማን ከየካ ክፍለ ከተማ አገናኝቷል ፤ ተመጣጣኝ ይመስል በነበረው በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች መካከል አስቆጪ የሚባል የግብ ሙከራዎች አልተደረጉም።ይልቁንስ ሁለቱም ጥንቃቄን አድርገው ለመጫወት የሞከሩበት አጋማሽ ነበር።
ነገርግን ሸገር ከተማዎች በ30ኛው ደቂቃ ያገኙትን አጋጣሚ በአላዛር ሽመልስ አማካኝነት ተጠቅመዉ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሮባቸዋል።
በሁለተኛው አጋማሽም ከመጀመሪያ ጋር በሚመሳል መልኩ የቀጠለ ቢሆንም ከመጀመሪያ አጋማሽ አንፃር መጠነኛ መሻሻሎችን ያሳዩት ሸገር ከተማዎች በ68ኛው ደቂቃ በፊት መስመር ተጫዋቻቸው በአላዛር ሽመልስ አማካኝነት አደገኛ ሙከራ አድርገው የግብ አግዳሚ መልሶባቸዋል።
በሂደት መልሶ ማጥቃትን አማራጫቸው ያደረጉ የሚመስሉት የካ ክፍለ ከተማዎች የተወሰኑ ዕድሎች በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች መፍጠር ችለዋል። በተለይም በ80ኛው ደቂቃ አምበላቸው ሚኪያስ አመሃ ጥሩ የግብ ሙከራ አድርጎ የሸገር ከተማው ግብ ጠባቂ ያዳነበት እንዲሁም በ85ኛው ደቂቃ ላይ የሸገር ከተማ ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት አደገኛ ቦታ ላይ ቅጣት ምት አግንተው ሳይጠቀሙ የቀረበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ናቸው።በዚህም ጨዋታው ያለ አሸናፊ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
በርከት ያሉ ጥፋቶች በተመለከትንበት የአምስት ሰዓቱ መርሃግብር ከፋ ቡናን ከኦሜድላ አገናኝቷል።ሁለቱም ቡድኖች ሃይል በቀላቀለ አቀራረብ ተደጋጋሚ የቆሙ ኳስ አጋጣሚዎችን በፈጠሩበት በዚሁ ጨዋታ በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ብቻ በርከት ያሉ የቆሙ ኳስ አጋጣሚዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተፈጠሩበት ነበር።
በ16ኛው ደቂቃ የከፋ ቡና ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት ቅጣት ምት ያገኙት ኦሜድላዎች 20 ቁጥር ለባሹ ቢኒያም ካሳሁን ኳሷን በቀጥታ ወደግብ መቷት ከመረብ ጋር ተገናኝታ መሪ መሆን ችለዋል።ተጨማሪ ግብ ፍለጋ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ የቀጠሉት ኦሜድላዎች በ25ኛው ደቂቃ በቻላቸው ቤዛ አማካኝነት አደገኛ ሙከራ ቢያደርጉም የከፋ ቡናው ግብ ጠባቂ አድኖበታል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ ይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወት የጀመሩት ከፋ ቡናዎች በ31ኛው ደቂቃ የኦሜድላ ከተማ ተከላካዮች ከግብ ጠባቂያቸው ጋር መግባባት ተስኗቸው የሰሩትን ስህተት በመጠቀም ሙሉቀን ተሾመ ኳሷን አግንቶ ወግብነት ቀይሮ አቻ እንዲሆኑ አስችሏል።
በመጀመሪያ አጋማሽ መደበኛው አርባ አምስት ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ላይ የከፋ ቡና ተጫዋቾች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ወደፊት ሲሄዱ የኦሜድላ ተከላካዮች ኳሱን አስጥለው በመልሶ ማጥቃት ሰይፈ ዛኪር ኳሱን አግኝቶ በግሉ እየነዳ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በመግባት ባስቆጠራት ግብ ኦሜዳላዎች ጨዋታውን 2ለ1 እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ኦሜድላዎች የተጫዋች ቅያሪን በማድረግ ይበልጥ ተሻሽለው ሲቀርቡ በዚህም በተለይ በ52ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ማሙሽ ድባሮ ከመስመር አክርሮ የመታት ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ ተመለሰችበት እንጂ መሪነታቸውን ለማሳደግ ቀርበው ነበር።
በአንፃሩ ከፋ ቡናዎችም አቻ ለመሆን በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን አስቆጪ ሚባለውን ሙከራ በ80ኛው ደቂቃ ተከላካዩ መታሰቢያ ገዛኸኝ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው መልሶበታል።
በቀሩት ደቂቃዎች ከፋ ቡና ለአቻነት ኦሜድላ ደግሞ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ የግብ ሙከራዎችን ቢያድርጉም ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 2ለ1 በሆነ ውጤት በኦሜድላ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በግብ ሙከራዎች የታጀበው የቀን ስምንት ሰዓቱ ጨዋታ ቢሾፍቱ ከተማን ከደብረብርሃን አገናኝቷል።
በመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን ያደረጉበት ሲሆን በ10ኛው ደቂቃ የብርሃናማዎቹ የፊት መስመር ተጨዋች ሄኖክ አየለ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረጋት ሙከራ ቀዳሚዋ ነበረች። በተጨማሪም በ25ኛው ደቂቃ ታደለ መንገሻ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት የሞከራት እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት ሙከራ ሌላዋ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
ቢሾፍቱ ከተማዎች በበኩላቸው አምበላቸው ነጋሽ ታደሰ ያመቻቸውን ኳስ ዳዊት ሽፈራው ያደረገው ሙከራ እንዲሁም በተጨማሪ ደቂቃ የመስመር ተከላካያቸው ደጋጋ በዳሶ ያደረጓቸው ሙከራዎች ለግብነት የቀረቡት ናቸው።
ከእረፍት መልስም ሁለቱም ቡድኖች በፉክክር የታጀበ አጋማሽ ያሳለፉ ቢሆንም በስተመጨረሻም ግን ጨዋታው ያለ አሸናፊ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የጨዋታ ዕለቱ ሆነ የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ የነበረው ጨዋታ አዲስከተማ ክ/ከተማን ከ ወሎ ኮምቦልቻ ያገናኘው ነበር።
መርሃግብር ግቦችን ማስመልከት የጀመረው ገና በማለዳ ነበር ፤ በ2ኛው ደቂቃ አዲስ ከተማዎች በቅብብል ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ያደረሱትን ኳስ ሰለሞን ጌዲዮን በጥሩ አጨራረስ በማስቆጠር አዲስ ከተማን መሪ አድርጓል።
በፍጥነት የተቆጠረባቸውን ግብ ለማካካስ መታተር የጀመሩት ወሎ ኮምቦልቻ የአዲስ ከተማን የግብ ክልል በተደጋጋሚ መጎብኘት ችለዋል።በ25ኛው ደቂቃ 14 ቁጥር ለባሹ ተካልኝ መስፍን ከግብ ክልል ውጪ ሆኖ አክርሮ በመምታት ያደረገው ጠንከራ ሙከራ በግብ ጠባቂ ተመለሰበት እንጂ አደገኛ ነበር።
ጥሩ ፉክክር በታየበት የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወሎ ኮምቦልቻዎች የአቻነቷን ግብ ፍለጋ በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል የደረሱበትም ነበር።በተለይም በ55ኛው ደቂቃ ቢላል ገመዳ ከግብ ከአዳስ ከተማ ግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ በጣም አስቆጭ ነበረች።
አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማዎች በአንፃሩ ውጤቱን ለማስጠበቅ በከፍተኛ ጥንቃቄ በመከላከል ያደረጉት ጥረት በስተመጨረሻም ውጤት አስገኝቶላቸው ጨዋተውን 1ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፈው መውጣት ችለዋል።