ሪፖርት | የጦና ንቦቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

ብርቱ ፉክክር በተደረገበት የሣምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ወልቂጤ ከተማን 2ለ1 ረቷል።

በሣምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ወላይታ ድቻ እና ወልቂጤ ከተማ ሲገናኙ ሊጉ ከመቋረጡ በፊት በነበረው ጨዋታ ወላይታ ድቻ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ከገጠመው ቡድኑ አንተነህ ጉግሳ እና ዘላለም አባተን በማሳረፍ አዛሪያስ አቤል እና ዮናታን ኤልያስን ሲጠቀሙ ወልቂጤ ከተማ በአንፃሩ ከመቻሉ ጨዋታ የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። አዳነ በላይነህ ፣ ተመስገን በጅሮንድ ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ ፣ ዳንኤል መቀጫ እና ዳንኤል ደምሱ ወጥተው በሳሙኤል ዳንኤል ፣ ጋዲሳ መብራቴ ፣ በቃሉ ገነነ ፣ ሙሉዓለም መስፍን እና አቡበከር ሳኒ ተተክተዋል።


በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ሲችሉ የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን የጦና ንቦቹ የተሻሉ ነበሩ። የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራም 9ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ጸጋዬ ብርሃኑ ከቢኒያም ፍቅሬ ተነስቶ ዮናታን ኤልያስ ሳይቆጣጠረው የቀረውን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ግብ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለው መልሶበታል።

እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት ሠራተኞቹ 20ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራቸውን አድርገዋል። ጋዲሳ መብራቴ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሙሉዓለም መስፍን በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ግሩም ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ጨዋታው 35ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በድቻዎች አማካኝነት ግብ ተቆጥሮበታል። ጸጋዬ ብርሃኑ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ፍቅሩ በድንቅ አጨራረስ የመታው ኳስ በተከላካይ ተጨርፎ መረቡ ላይ አርፏል።

ወልቂጤዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላም የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መታተራቸውን ቀጥለው 39ኛው ደቂቃ ላይ በበቃሉ ገነነ አማካኝነት በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል የወጣ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ሆኖም አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ የጦና ንቦቹ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ቢኒያም ፍቅሩ በተረከዝ በመምታት በቄንጥ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ብዙዓየሁ ሰይፉ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለው ይዞበት የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከዕረፍት መልስ ድንቅ አጀማመር ያደረጉት ወልቂጤዎች 48ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ጋዲሳ መብራቴ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ የድቻ ተከላካዮች በአግባቡ ሳያግዱት ቀርተው ኳሱን ያገኘው አቡበከር ሳኒ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ግብ አስቆጣሪው አቡበከር ከደቂቃዎች በኋላም ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ተጨማሪ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ይዞበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ በመጠኑ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ወላይታ ድቻዎች በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች በድጋሚ ወደ ጋለ እንቅስቃሴ በመመለስ 75ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ኢዮብ ተስፋዬ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ብዙዓየሁ ሰይፉ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለው በጥሩ ቅልጥፍና መልሶበታል።

በሚያገኙት ኳስ በፈጣን የማጥቃት ሸግግር የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ መስመር በተደጋጋሚ መፈተን የቻሉት የጦና ንቦቹ 78ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። አብነት ደምሴ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በአስደናቂ ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት በግቡ የቀኝ የላይ ክፍል መረቡ ላይ አሳርፎታል። ግቡ በተቆጠረበት ቅጽበትም በተፈጠረ ሰጣ ገባ የወልቂጤ ከተማው አምበል ሳምሶን ጥላሁን በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

አጋማሹን ከጀመሩበት ግለት እየተቀዛቀዙ የሄዱት ሠራተኞቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በድጋሚ መነቃቃት ሲችሉ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 5 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ሳይቆጣጠረው የቀረውን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው አሜ መሐመድ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ራምኬል ሎክ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበት ወርቃውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።