ሪፖርት | እጅግ ቀዝቃዛው ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል

ለተመልካች ሳቢ ያልነበረው የሲዳማ ቡና እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ 0-0 ተጠናቋል።

በምሽቱ መርሐግብር ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ መድን ላይ በአዲሱ አሰልጣኝ ስር ድል ከቀናው ስብስቡ ሀብታሙ ገዛኸኝን በሙሉቀን አዲሱ ፤ ማይክል  ኪፖሩልን በቡልቻ ሹራ መተካት ሲችሉ በሀድያ ሆሳዕና ተረተው የነበሩት አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ አልያስ ለገሠን አሳርፈው አቡበከር ሻሚልን በማስገባት ለጨዋታው ቀርበዋል።

12፡00 ላይ በተጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የግብ ዕድል ያልተፈጠረበት ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ ግን አዳማዎች ብልጫውን ወስደዋል። የጨዋታው የመጀመሪያ የተሻለ ሙከራም 14ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ የአዳማው ዮሴፍ ታረቀኝ ከሳጥን ጠርዝ በግሩም ሁኔታ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቷል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የተወሰደባቸው እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተደራጅተው ለመግባት የተቸገሩት ሲዳማዎች 16ኛው ደቂቃ ላይ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገው በዛብህ መለዮ እና ይገዙ ቦጋለ ሊያደርጉት የነበረውን ሙከራ ተከላካዮች ተረባርበው አግደውባቸዋል።

እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር በሚያደርጉት ዝግ ያለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በተቸገሩት አዳማዎች በኩል ዮሴፍ ታረቀኝ 21ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ 33ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከቅጣት ምት ያደረጋቸው እና በግቡ አግዳሚ ለጥቂት የወጡት ኳሶች ተጠቃሽ ነበሩ።

 

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በሁለቱም በኩል ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተደርጎበታል። ሆኖም በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ የነበራቸው አዳማዎች 59ኛው ደቂቃ ላይ የአጋማሹን የተሻለ የመጀመሪያ የጠራ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ አህመድ ረሺድ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ዮሴፍ ታረቀኝ ያደረገውን ሙከራ የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ በቀላሉ ይዞበታል።

በቀሪ ደቂቃዎችም ጨዋታው በተደጋጋሚ በተለይም በሲዳማ ተጫዋቾች አማካኝነት በሚደረጉ ጉሽሚያዎች አሰልቺ እየሆነ ሲሄድ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ቢኖራቸውም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በቁጥር በዝተው ለመድረስ የተቸገሩት ሲዳማዎችም አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ሲቀሩ በአዳማዎች በኩል ግን 93ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ረሺድ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ አስወጥቶበታል። ጨዋታውም 0-0 ተጠናቋል።