ሪፖርት | ኃይቆቹ አምስተኛ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደዋል

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ መቻል ሀዋሳን 2-1 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር መቻል እና ሀዋሳ ከተማ ሲገናኙ ካለፈው ሳምንት ጨዋታቸው ሀዋሳ ከተማ በኢትዮጵያ ቡና ሲሸነፍ ከተጠቀመው አሰላለፍ በቀይ ካርድ በወጣው መድኃኔ ብርሃኔ እንየው ካሳሁንን ፣ በአብዱልባሲጥ ከማል አማኑኤል ጎበናን እና በሲሳይ ጋቾ ሚሊዮን ሰለሞንን ሲተኳቸው መቻሎች ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ከነዓን ማርክነህን እና በረከት ደስታን አሳርፈው በአቤል ነጋሽ እና ሳሙኤል ሳሊሶ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።

9 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢደረግም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን መቻሎች የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም ግን የመጀመሪያው ለግብ የቀረበ ሙከራ 11ኛው ደቂቃ ላይ በኃይቆቹ አማካኝነት ሲደረግ እንየው ካሳሁን በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ያገኘው አማኑኤል ጎበና በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቶ የግብ ዕድሉን አባክኖታል።

በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቀጠሉት መቻሎች 24ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ሳሙኤል ሳሊሶ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ አስወጥቶበታል። ያንኑ ኳስ ራሱ ሳሙኤል ሳሊሶ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ሲያሻማው ኳሱን ያገኘው ምንይሉ ወንድሙ በግንባር ገጭቶ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በኳስ ቁጥጥሩ ፍጹም ብልጫ በመውሰድ የአቻነት ግብ ፍለጋ መታተራቸውን የቀጠሉት ሀዋሳዎች 30ኛው ደቂቃ ላይ በዓሊ ሱሌይማን አማካኝነት ከሳጥን አጠገብ ጥሩ ሙከራ አድርገው በግቡ አግዳሚ ለጥቂት ሲወጣባቸው 45ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። አዲሱ አቱላ ከቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ሲመልስበት የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ዓሊ ሱሌይማን ወደ ግብ የመታውን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ በጥሩ ቅልጥፍና ከመስመር አግዶበታል።


ከዕረፍት መልስ በተሻለ መረጋጋት ጨዋታውን የጀመሩት መቻሎች 48ኛው ደቂቃ ላይ የአጋማሹን የመጀመሪያ የጠራ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ሽመልስ በቀለ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ስቴፈን ባዱ አኖርኬ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበት አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በሁለተኛው አጋማሽም ዘግየት ብለው ወደ ተሻለ የጨዋታ ግለት የገቡት ሀዋሳዎች የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ መጫወታቸውን ሲቀጥሉ 64ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። አዲሱ አቱላ በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ዓሊ ሱሌይማን በፍጥነት ደርሶ በግሩም ቅልጥፍና መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በድጋሚ በማንሠራራት ተጭነው የተጫወቱት መቻሎች 78ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ሽመልስ በቀለ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ ያደረገው ግሩም ሙከራ በግቡ አግዳሚ ሲመለስበት በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ግን ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሽመልስ በቀለ ያቀበለውን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ከነዓን ማርክነህ አስቆጥሮታል። በቀሪ ደቂቃዎችም መጠነኛ ፉክክር ተደርጎ 91ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳው ዓሊ ሱሌይማን ከአማኑኤል ጎበና በተመቻቸለት ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቶ የግብ ዕድሉን ሲያባክነው ጨዋታውም በመቻል 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።