የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 11ኛ ሳምንት ዛሬ ሲጠናቀቅ በምድብ ‘ሀ’ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸንፎ ተከታዩ አዲስ አበባ ከተማ ነጥብ ሲጥል በምድብ ‘ለ’ ሸገር ከተማ ከመሪዎቹ ጋር ያለውን ልዩነት አጥብቧል።
በ11ኛ የጨዋታ ሳምንት 2ኛ ቀን የመጀመሪያ የነበረው መርሃግብር ቦዲቲ ከተማን ከካፋ ቡና ያገናኘ ነበር። በመጀመሪያ አጋማሽ በቦዲቲ ከተማ የተሻለ ቁጥጥር እና የግብ ሙከራዎችን ያደረጉበት ነበር በተለይም በ22ኛው ደቂቃ ሙሉቀን ተስፋዬ ከቀኝ መስመር በቀጥታ ወደ ግብ የላካት እና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
ካፋ ቡና በአንፃሩ አልፎ አልፎ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በ35ኛው ደቂቃ መታሰቢያ ገዛኸኝ በቦዲቲ ከተማው የፊት መስመር ተጨዋች በሆነው ማሞ አየለ ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣቱ በጎዶሎ ተጫዋች ቀሪውን ደቂቃ ለመጫወት ተገደዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ካፋ ቡና በቁጥር ማነሳቸውን ለመጠቀም ቦዲቲ ከተማዎች ይበልጥ ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን ፤ ይህም ጥረታቸው በ55ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቶ አምበላቸው ሳምሶን ደጀኔ መሬት ለመሬት ያቀበለውን ኳስ ኤፍሬም አበራ አግኝቶ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሯታል።
በዚህ ያላበቁት ቦዲቲዎች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ቦዲቲ ከተማዎች ጥረታቸውን አጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን ለአብነትም በ75ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አበራ በአንድ ለአንድ ተቀባብለው ከግራ መስመር አከባቢ የመታት ኳስ የግብ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
በአንፃሩ ካፋ ቡናዎች ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ጥረት ቢያደርጉም ተቀይሮ የገባው በቃሉ ተካ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ካደረጋቸው ሁለት አደገኛ ሙከራዎች ውጭ ውጤቱን ለመቀየር የሚያስችል በቂ ጥረት ሳያሳዩ ጨዋታው በቦዲቲ ከተማ የ1ለ0 “አሸናፊነት ተገባዷል።
ምድብ ‘ሀ’ ረፋድ ላይ በተከናወነው ጨዋታ ጅማ አባ ቡና እና ቤንች ማጂ ቡና 1-1 ተለያይተዋል። በውጤቱም ቤንች ማጂ ቡና በንብ የተወሰደበትን የሦስተኝነት ደረጃ ማስመለስ ሳይችል ቀርሯል።
ለዕለቱ ሁለተኛ በነበረው እና ከጅምሩ በበርካታ የግብ ሙከራዎች በታጀበው የአምስት ሰዓቱ ጨዋታ ደብረብርሃን ከተማ ከአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ያገናኘ ነበር።
በመጀመሪያዎቹ በአስር ደቂቃዎች ብቻ በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች ባስመለከተን ጨዋታ በደብረ ብርሃን በኩል በ3ኛው ደቂቃ ኡስማን መሐመድ ከሳጥን ውጪ የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂው እንደምንም ሲያድንበት በ5ኛው ደቂቃ ደግሞ ታደለ መንገሻ ከመስመር ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ ሄኖክ አየለ ወደ ግብ ቢመታትም ተከላካዮች ተረባርበው አድነውታል።
አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማዎች በአንፃሩ በ8ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ተከላካዩ ሰለሞን ብሩ በረጅሙ ያወጣትን ኳስ ሰለሞን ጌዲዮን አግኝቶ ከተቃራኒ ግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።ሌላናው ለግብ የተቃረበ ሙከራ የመስመር ተከላካይ የሆነው ጳውሎስ ካንቲባ በግራ መስመር ሆኖ የመታትን ኳስ የግብ አግዳሚ መልሶበታል።
ያለግብ ከተጠናቀቀው የመጀመሪያ አጋማሽ በኃላ ሁለቱም ቡድኖች ከመልበሻ ቤት መልስ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ተሽሎ ለመመለስ ጥረት አድርገዋል።በ55ኛው ደቂቃ የአዲስ ከተማው ሰለሞን ጌዲዮን ያቀበለውን ኳስ ቅዱስ ተስፋዬ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጭ በሚል የተሻረበት ሲሆን በ57ኛው ደቂቃ ግን ደብረብርሃኖች ቀዳሚ መሆን ችለዋል ፤ ወንደሰን ሽፈራው ከቀኝ መስመር የመታት ኳስ ወደግብነት ተቀይራ መሪ እንዲሆኑ አስችላለች።
የአቻነት ግብ ፍለጋ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት አዲስ ከተማዎች ብዙ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።ጥረታቸው በስተመጨረሻም ፍሬ አፍርቶ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ 3 ደቂቃ ሲቀር ቦጃ አንዳታ ከርቀት መጥቶ በማስቆጠር ጨዋታው 1ለ1 እንዲሆኑ ቢያስችልም መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጡ ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ የማዕዘን ምት ያገኙት ደብረብርሃኖቹ በ90+3 ላይ ከማዕዘን የተሻማውን የመጨረሻ እድል በመጠቀም ልደቱ ጌታቸው በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሮ ጨዋታውን ደብረብርሃን ከተማ 2ለ1 እንዲያሸንፍ አድርጓል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ምድብ ‘ሀ’ ባስተናገደው ጨዋታ ግርጌ ላ ይ የሚገኘው ኮልፌ ቀራኒዮ በዮናስ ወልደ ብቸኛ ጎል ስልጤ ወራቤን በመርታት የዓመቱን የመጀመሪያ ድል አሳክቷል።
በማስከተል ቀን ስምንት ሰዓት ላይ የተካሄደው መርሃ ግብር ወሎ ኮምቦልቻን ከየካ ክ/ከተማ አገናኝቷል።
በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ አጀማመርን ለማድረግ የሞከሩት የካዎች ገና ጨዋታው በጀመረ በ2ኛው ደቂቃ ያገኙትን የቅጣት ምት አጋጣሚ የመስመር ተመላላሻቸው ጌታሁን አየለ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ኳስና መረብ አገናኝቷል።
ከግቧ በኋላ በብዙ መልኩ የተቀዛቀዙት የካዎች በአጋማሹ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ፍፁም ደካማ ነበር።
በአንፃሩ ወሎ ኮምቦልቻዎች ደግሞ የአቻነት ግብ ፍለጋ ጫና ፈጥረው ሲጫውቱ በዚህም ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል። በተለይም በ36ኛው ደቂቃ የወሎ ኮምቦልቻው ኪሮስ ጌታቸው ያሻገራለት ኳስ ዮሀንስ ሳይጠቀምባት ቀረ እንጂ ሁለቱ ቡድኖች ነጥብ ተጋርተው ወደ ዕረፍት ባመሩ ነበር።
ምንም እንኳን እየመሩ እረፍት ቢወጡም በሁለተኛው አጋማሽ የካ ክ/ከተማ ቀዝቀዝ ያለ የጨዋታ እንቅስቃሴ አስመልክተዋል። ወሎ ኮምቦልቻ በአንፃሩ የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ የተጫወቱ ሲሆን በተለይም በ75ኛው ደቂቃ ማኑሄ ጌታቸው እና ቢላል ገመዳ በአንድ ሁለት ቅብብል በኃላ ያደረጉትን ሙከራ ግብ ጠባቂ አድኖባቸዋል።
ቀዝቀዝ ብለው የተስተዋሉት የካዎች በ81ኛው ደቂቃ ላይ ብስራት ታምራት በራሱ ጥረት ኳስን ይዞ በመግባት ሁለተኛ ግብ ለቡድኑ አስቆጥሮ ጨዋታው 2ለ0 በሆነ ውጤት በየካ ክ/ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በምድብ ‘ሀ’ መሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሞጆ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ አቤል ሐብታሙ እና ናትናኤል ሰለሞን በሁለቱ አጋማሾች ማብቂ ያ ላይ ባስቆጠሯቸው ጎሎች2- 0 ማሸነፍ ችሏል። በውጤቱም ነጥቡን 25 በማድረስ መሪነቱን አስቀጥሏል።
ለተመልካች ሳቢ የነበረው የምድብ “ለ” የሳምንቱ የመጨረሻ መርሃግብር ኦሜድላን ከሸገር ከተማ አገናኝቷል።
በጨዋታው ገና ከጅምሩ የበላይነት ይዘው የተጫወቱት ሸገር ከተማዎች በብዙ መልኩ የተሻሉ ነበሩ።በ5ኛው ደቂቃ ዘነበ ከድር ከመስመር ባሻገራት እና ፋሲል አስማማው ባደረጋት ሙከራ የተጋጣሚን የግብ ክልል መጎብኘት የጀመሩ ሲሆን በ8ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ሀይከን ድማሙ በቀላሉ ማስቆጠር የሚችለውን አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ብልጫ የተወሰደባቸው ኦሜድላዎች በአንፃሩ በሂደት በመልሶ ማጥቃት አደገኛ ሙከራዎችን በተደጋጋሚ አድርገዋል።በተለይም በ20ኛው ደቂቃ በቻላቸው ቤዛ እንዲሁም በ26ኛው ደቂቃ ደግሞ በሰይፈ ዛኪር አማካኝነት ቢያደርጉም ጥረታቸው ሳይሰምር ቀርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የገቡት ሸገር ከተማዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ ችለዋል።በ62ኛው ደቂቃም ሸገሮች ያገኙትን የቅጣት ምት ኳስ ዘነበ ከድር በግሩም ሁኔታ ያሻማውን ኳስ የፊት መስመር ተሰላፊው ፋሲል አስማማው በግንባሩ በመግጨት ኳስና መረብን አገናኝቶ ሸገርን መሪ አድርጓል።
በደቂቃዎች ልዩነት ሸገሮች ሁለተኛ ግባቸውን ለማግኘት ተቃርበው ነበር።ሀይከን ድማሙ እና ፋሲል አስማማው በመቀባበል ያደረጉት ሙከራ የግብ አግዳሚ መልሶባቸዋል።
በተመሳሳይ በ85ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ግብ አስቆጣሪው ፋሲል አስማማው በሚገርም ሁኔታ የሞከራት ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል ፤ ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በሸገር ከተማ የ1ለ0 የበላይነት ተጠናቋል።
በምድብ ሀ የማሳረጊያ ጨዋታ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ከወልዲያ ነጥብ መጋራቱን ተከትሎ ከመሪው ሁለት ነጥብ ርቀት ላይ ለመቀመጥ ተገዷል።