ቀዝቃዛ የነበረው የባህር ዳር ከተማ እና የሀምበርቾ ጨዋታ 0-0 ተጠናቋል።
በምሽቱ መርሐግብር ባህር ዳር ከተማ እና ሀምበርቾ ሲገናኙ የጣና ሞገዶቹ ከሻሸመኔ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስባቸው የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ፍሬዘር ካሳ እና ፍቅረሚካኤል ዓለሙ አርፈው አብዱላዚዝ ሲያሆኔ እና አለልኝ አዘነ ሲተኳቸው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት አስተናግደው የነበሩት ሀምበርቾዎች በበኩላቸው የስድስት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገዋል። ምንያምር ጴጥሮስ ፣ ታዬ ወርቁ ፣ ተመስገን አሰፋ ፣ በፍቃዱ አስረሳኸኝ ፣ አፍቅሮት ሠለሞን እና በረከት ወንደሙን አሳርፈው በትዕግስቱ አበራ ፣ ብሩክ ቃልቦሬ ፣ አቤል ከበደ ፣ የኋላሸት ፍቃዱ ቶሎሳ ንጉሤ እና ኤፍሬም ዘካርያስ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።
12 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ባህር ዳሮች ለኳስ ቁጥጥሩ ቅድሚያ በመስጠት እና ከፍተኛ ብልጫም በመውሰድ ዝግ ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመጫወት ሲሞክሩ ሀምበርቾዎች በአንጻሩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በሚያገኙት ኳስ የመልሶ ማጥቃት እንቅሰቃሴ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል።
በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት የጣና ሞገዶቹ 9ኛው ደቂቃ ላይ በስድስተኛ የማዕዘን ምታቸው የአጋማሹን የተሻለ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ መሳይ አገኘሁ ከግራ መስመር ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ታደሰ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ በድንቅ ቅልጥፍና መልሶበታል።
በጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ለተጋጣሚ ፈታኝ ሆነው የቀረቡት ሀምበርቾዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ ወሳኝ ተጫዋቻቸውን ብሩክ ቃልቦሬን ከዳኛው ጋር በተፈጠረ እሰጥ አገባ በቀይ ካርድ አጥተዋል። ሆኖም የተጫዋች የቁጥር ብልጫ ያገኙት የጣና ሞገዶቹ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስም ጨዋታው ተመሳሳይ በሆነ ሂደት ሲቀጥል መሳይ አገኘሁን አስወጥተው በረከት ጥጋቡን በማስገባት አሰላለፋቸውን በሚያጠቁበት ሰዓት ወደ 3-4-3 እየቀየሩ መጫወትን የመረጡት ባህር ዳር ከተማዎች 56ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ፍጹም ጥላሁን ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ከተከላካይ ጋር ታግሎ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ታደሰ መሬት ለመሬት በመምታት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ በጥሩ ብቃት ይዞበታል።
ጨዋታው ይበልጥ እየተቀዛቀዘ ሲሄድ በቀጣይ ደቂቃዎችም ሀምበሪቾዎች ጨዋታውን በማረጋጋት ከጨዋታው ነጥብ ለማግኘት ጥረታቸውን አጠናክረው ሲቀጥሉ የጣና ሞገዶቹ በአንጻሩ በቁጥር እየበዙ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቢደርሱም አለልኝ አዘነ ፣ ቸርነት ጉግሣ እና ሀብታሙ ታደሰ ከሳጥን ውጪ ካደረጓቸው ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ውጪ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲቸገሩ ተስተውሏል። 82ኛው ደቂቃ ላይም በሀምበርቾ በኩል ቅጣት ላይ የነበረው ቴዎድሮስ በቀለ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ በአቤል ከበደ ተቀይሮ በመግባት ወደ ሜዳ ተመልሷል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም ባህር ዳሮች በኳስ ቁጥጥሩ ፍጹም ብልጫ በመውሰድ መታተራቸውን ቢቀጥሉም 86ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ሱሌይማን ትራኦሬ ከዓባይነህ ፌኖ በተቀበለው ኳስ ያደረገው በግቡ የግራ ቋሚ በኩል የወጣው ሙከራ የተሻለው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታውም 0-0 ተጠናቋል። ውጤቱም ሀምበሪቾ ከተከታታም አምስት ሽንፈቶች በኋላ ነጥብ ያገኘበት ሆኗል።